"ሽግግሩ በስፋት አሳታፊ ካልሆነ ሌላ ግጭት ሊከተል ይችላል" በሦሪያ የተመድ ልዩ ልዑክ

  • ቪኦኤ ዜና

ፎቶ ፋይል፦ በሦሪያ የተመድ ልዩ ልዑክ ጌይር ፐደርሰን

የፕሬዝደንት ባሻር አል አሳድን ከሥልጣን መወገድ ተከትሎ ሦሪያ ላይ የተደቀነው ትልቁ ፈተና የፖለቲካ ሥልጣን ሽግግሩ አደረጃጀት እና አፈጻጸም መሆኑን በሦሪያ የተመድ ልዩ ልዑክ ተናገሩ።

ጌይር ፐደርሰን ዛሬ ማክሰኞ ጄኔቫ ላይ ለጋዜጠኞች በሰጡት ቃል ሦሪያ "ደማስቆ ላይ ኅብረተሰቡን በስፋት የሚወክል ተዓማኒ የሆነ ሽግግር ማደራጀት ያስፈልጋታል" ብለዋል።

በዚህ መንገድ የሥልጣን ሽግግሩ ከተከናወነ ዓለም አቀፍ ማዕቀቦች እንዲነሱ እና ስደተኞች ወደቀያቸው እንዲመለሱ የሚያስችል ሁኔታ ሊፈጠር ይችላል ያሉት ልዩ ልዑኩ ያ ካልሆነ ግን ሌላ ግጭት አደጋ ሊደቀን እንደሚችል ተናግረዋል።

Your browser doesn’t support HTML5

የሶሪያው ባሻር አል አሳድ አገዛዝ መውደቅ እና ዓለም አቀፋዊ አና ቀጣናዊ ውጤቱ  ሲተነተን

ይህ በእንዲህ እንዳለ የሦሪያ አማጺያን አዛዥ አህመድ አል ሻራአ በሰፊው በሚታወቁበት ስማቸው አቡ መሐመድ አል ጎላኒ ዛሬ በሰጡት ቃል ሦሪያዊያን ላይ ሰቆቃ በመፈጸም እጃቸው ያለበትን የተወገደው የአሳድ መንግሥት ከፍተኛ ባለሥልጣናት ስም ዝርዝር ይፋ እናደርጋለን ብለዋል። በጦር ወንጀል የተሳተፉ ከፍተኛ የጦር ሠራዊት እና የደሕንነት ባለሥልጣናትን መረጃ ለሚሰጥ ወሮታ እንከፍላለን ሲሉም አክለዋል።

የጀርመን ቻንስለር ኦላፍ ሾልዝ እና የፈረንሳይ ፕሬዚደንት ኢማኑዌል ማክሮንየአሳድ አገዛዝ መውደቁን በደስታ ተቀብለው ከአዲሶቹ መሪዎች ጋር የመሠረታዊ ሰብዓዊ መብቶች ከበሬታ እና የውህዳን ብሔረሰቦች እና የሃይማኖት ተከታዮችን ደሕንነት ተመርኩዘን አብረን ለመስራት ዝግጁ ነን ማለታቸውን ትላንት የጀርመን መንግሥት ያወጣው መግለጫ አመልክቷል።

በሌላ በኩል የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት እስራኤል ከጦር ነጻ የጎላን ኮረብቶች አካባቢ አልፋ ወታደሮቿን ማስገባቷ እንዳሳሰበው አስታውቋል። እስራኤል "ጸጥታዬን ለማስከበር አስፈላጊ በመሆኑ ነው" ብላለች።

ዛሬም ደማስቆ አካባቢ የቦምብ ጥቃት መካሄዱን ዘገባዎች አመልክተዋል። ትላንት የእስራኤል የውጪ ጉዳይ ሚንስትር ጊዲዮን ስታር ሲናገሩ ኬሚካል የጦር መሣሪያዎች እና ረጅም ርቀት ሚሳይሎች የተከማቹበት ተብለው የተጠረጠሩ ቦታዎችን መሣሪያዎቹ ጠላት ኅይሎች እጅ እንዳይገቡ ለመከላከል በሚል ኅይሎቻችን ደብድበዋል ሲሉ አስታውቀዋል። ሳውዲ አረቢያ የእስራኤልን እርምጃ አውግዛለች።

ይህ በእንዲህ እንዳለ የአማጺያኑ መሪ ጎላኒ የሥልጣን ርክክቡን ሂደት ለማቀናጀት ትላንት ለመጀመሪያ ጊዜ ከተሰናባቹ ጠቅላይ ሚኒስትር መሐመድ ጄላሊ ጋር ተገናኝተው መነጋገራቸውን አማጽያኑ አስታውቀዋል።

በመንግሥታቱ ድርጅት የአሳድ መንግሥት ተሹዋሚው አምባሳደር በአዲሶቹ ሥራችንን እንድንቀጥል መመሪያ ተሰጥቶናል ሲሉ አስታውቀዋል። የጸጥታ ምክር ቤቱ ትላንት ማታ በሩሲያ ጥያቄ በዝግ ተሰብስቦ በሦሪያ ጉዳይ ተወያይቷል።