የሱዳን ተፋላሚዎች የሰባት ቀናት ተኩስ ማቆም እንደሚያደርጉ አስታወቁ

  • ቪኦኤ ዜና
ካርቱም፣ ሱዳን

ካርቱም፣ ሱዳን

የሱዳን ተፋላሚ ኃይሎች ለሰባት ቀናት የሚቆይ ተኩስ ማቆም እንደሚያደርጉ ሲያሳውቁ፣ ዓለም ዜናውን በደስታ ተቀብሏል፡፡ ከሁለት ሣምንታት በላይ በተደረገው ውጊያ በመቶ የሚቆጠሩ ሲሞቱ፣ ሚሊዮኖችን ለዕለት ተዕለት ጉዳይ መንቀሳቀስ እንዳይችሉ አድርጓል፡፡

ተቀናቃኞቹ የሱዳን ጦር ጠቅላይ አዛዥ ጀኔራል አብደል ፈታህ አል ቡርሃን እና የፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ መሪ ጀኔራል ሞሃመድ አምዳን ዳጋሎ ወይም ኽመቲ ትናንት ማክሰኞ ለሰባት ቀናት የሚቆይ ተኩስ ማቆም እንደሚያደርጉ አስታውቀዋል፡፡

የአሜሪካው የውጪ ጉዳይ መሥሪያቤት ተኩስ ማቆም ላይ እንዲደረስ ለሳምንታት ጥረት ሲያደርግ እንደነበር ሲያስታውቅ፣ ዋይት ሃውስ ጉዳዩን በቅርብ እየተከታተለውና ከወታደራዊም ሆነ ከሲል መሪዎች ጋር እየመከረ እንደሆነ አስታውቋል፡፡

በሌላ በኩል የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰብዓዊ ጉዳዮች ሃላፊ ዛሬ በሱዳን ዋናው የባህር ወደብ ሲደርሱ፣ በተቃራኒው በሺሕ የሚቆጠሩ ሱዳናውያንና የውጭ አገር ዜጎች በግጭት ከታመሰችው አገር ለመውጣት ሲጠባበቁ ተስተውሏል፡፡

የመንግስታቱ ድርጅት የሰብዓዊ ጉዳዮችና የአስቸኳይ ዕርዳታ አስተባባሪ የሆኑት ማርቲን ግሪፊትስ በፖርት ሱዳን የተገኙት ተመድ ለሱዳን ሕዝብ ያለውን ቁርጠኝነት ለማሳየት መሆኑን በትዊተር በላኩት መልዕክት አስታውቀዋል፡፡

ግሪፊትስ በሱዳን የተገኙት ለሦስት ቀናት እንዲከበር የታቀደው የተኩስ ማቆም በሚያበቃበት ዕለት ነው፡፡ ተኩስ ማቆሙ ሳይከበር ቀርቶ ተፋላሚ ወገኖቹ ላለፉት ሶስት ቀናትም ውጊያቸውን ቀጥለዋል፡፡

በሁለቱ ተቀናቃኝ ጄኔራል ኃይሎች መካከል ግጭቱ ሚያዚያ 7 ቀን በጀመረ ከሳምንት በኋላ በሺሕ የሚቆጠሩ የተመድ ሠራተኞች ወደ ፖርት ሱዳን ሸሽተዋል፡፡

በግጭቱ እስከ አሁን 550 ሰዎች እንደሞቱ ሲነገር፣ 4 ሺህ 900 ሰዎች ደግሞ ተጎድተዋል፡፡ 334 ሺሕ የሚሆኑ ሱዳናውያን ወደ አካባቢው አገሮች ግብጽ፣ ቻድ፣ ደቡብ ሱዳን፣ ማዕከላዊ አፍሪካ ሪፐብሊክ፣ እና ኢትዮጵያ ተሰደዋል፡፡

ትናንት ማምሻውን በወታደራዊው ዋና መሥሪያ ቤት፣ በዓለም አቀፍ አውሮፕላን ጣቢያ እና በሪፐብሊካን ቤተ መንግሥት ውጊያው ሲቀጥል፣ የካርቱም ሠማይ በጭስ ሲሸፈን እና የጦር አውሮፕላኖች ሲበሩ ተስተውሏል ሲል አሶስዬትድ ፕረስ በዘገባው አመልክቷል፡፡

በሺሕ የሚቆጠሩ ሱዳናውያን የግብጽ ከተማ በሆነችው አስዋን በመግባት ላይ ይገኛሉ፡፡

ግጭቱ ከጀመረ አንስቶ 42 ሺህ ሱዳናውያንና 2 ሺሕ 300 የውጭ አገር ዜጎች ግብጽ ገብተዋል፡፡