በሱዳን ጦርነት የተገደሉት ሰዎች ቁጥር ከቀደሙት እጅግ የላቀ መሆኑ አንድ ጥናት አመለከተ

  • ቪኦኤ ዜና

በሱዳኑ እርስ በርስ ጦርነት የተገደሉት ሰዎች ቁጥር ቀደም ሲል ከተሰጠውም ግምት በእጅጉ የላቀ መሆኑን አንድ ዐዲስ ጥናት አመለከተ። በግጭቱም ሳቢያ በዓለም ከሁሉ የከፋው መኾኑ በተነገረለት የሱዳኑ ድርቅ ምክኒያት "በብዙ ሚሊዮን የሚገመቱ ሰዎች የረሃብ ቸነፈር አፋፍ ላይ ናቸው" ሲሉ የረድኤት ድርጅቶች አስጠንቅቀዋል።

የለንደኑ የኅብረተሰብ ጤና አጠባበቅ እና "የቆላማ አካባቢዎችን የሚያጠቁ (ትሮፒካል) በሽታዎች ጥናት ትምህርት ተቋም እንዳመለከተው፤ በካርቱም ግዛት ብቻ የተገደሉት ሰዎች ከዚህ ቀደም በመላዋ ሀገሪቱ በጦርነቱ ለተገደሉት ሰዎች ብዛት ከተሰጡት ግምቶችም የላቀ ነው።

“በካርቱም ግዛት፣ እንደ አውሮፓውያን የዘመን አቆጣጠር ከሚያዝያ 2023 እስከ ሰኔ 2024 በነበረው ጊዜ ውስጥ ቁጥሩ ከ61 ሺህ በላይ የሚደርስ ሰው በተለያዩ ምክንያቶች ለኅልፈት ተዳርጓል” የሚል ግምት አላቸው። ይህም ከጦርነቱ በፊት ከነበረው አሃዝ 50 በመቶ ከፍ ያለ ነው።

በዚሁ ተመሳሳይ ጊዜ በጦርነቱ የተነሳ በካርቱም ግዛት ብቻ ከ26 ሺህ በላይ ሰዎች መገደላቸውን ጥናቱ ጠቁሟል። ይህም በዓለም አቀፍ ደረጃ ግጭቶችን እና ያደረሱትን ጉዳት የሚከታተለው የበጎ አድራጎት ተቋም በመላዋ ሱዳን “ኾን ተብለው በተፈጸሙ ጥቃቶች ሳቢያ ጉዳት የደረሰባቸው ሰዎች’ በሚል ቀደም ሲል ካቀረበው 20 ሺህ 178 ከሚደርሰው የሟቾች ቁጥርም በእጅጉ የላቀ ነው” ሲል ሪፖርቱ አመልክቷል።

በለንደኑ የኅብረተሰብ ጤና አጠባበቅ እና የቆላማ አካባቢዎች (ትሮፒካል) በሽታዎች ጥናት ትምህርት ተቋም የቀረበው ሪፖርት ጨምሮ እንዳሳየው የአብዛኞቹ የእነኚህ ሞቶች ዋነኛ መንስኤ "ለመከላከል የሚቻሉ በሽታዎች እና ከፍተኛ ረሃብ" ናቸው። በዚህም መሠረት በሱዳን ጦርነቱን ጨምሮ በተለያዩ ምክኒያቶች ለሕልፈት የተዳረጉት ዜጎች አጠቃላይ ቁጥር ከቀደመው ግምት በብዙ የላቀ ሲሆን፤ “በካርቱም ግዛት ብቻ በሁሉም ዓይነት መንስኤዎች ከሞቱት ከ90 በመቶው በላይ አልተመዘገቡም” ሲል አብራርቷል።

እንደ አውሮፓውያን የዘመን አቆጣጠር በሚያዝያ 2023 ዓም የተቀሰቀሰው እና በሱዳን መንግሥት ኃይሎች እና በፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ መካከል የተፈጠረ ግጭት የተመላ የሥልጣን ሽኩቻ መላውን የሃገሪቱ ማህበረሰቦች አጠቃላይ ግንኙነቶች ያቋረጠ ሲሆን፤ በአብዛኞቹ የመንግሥት አገልግሎቶች ላይም ከፍተኛ ውድመት በማደረሱ በግጭቱ ሳቢያ የሞቱትን ሰዎች ቁጥር በትክክል ለማወቅ አዳጋች አድርጎታል።

ጥናቱ ከበርካታ ምንጮች የተገኙ መረጃዎችን በማነፃፀር፣ ምንም ዓይነት መረጃ በማይገኝበት ጊዜ ከትክክለኛው ግምት ላይ ለመድረስ የሚያስችል "አዲስ" የሚሰኝ የጥናት ዘዴ መጠቀሙ ተገልጿል።