ሱዳን የሙያ ስነምግባር ያልጠበቁ ዘገባዎችን የሚያቀርቡ እና ፈቃዳቸውን ያላደሱ ያለቻቸውን ሦስት የአረብ ሳተላይት ጣቢያዎች ትናንት ማክሰኞ አግዳለች፡፡
የባህልና ማስታወቂያ ሚኒስቴሩ ያገዳቸው፣ ንብረትነታቸው የሳዑዲ አረብያ መንግሥት የሆኑ አል አረብያ እና አል ሀዳት የተባሉ ሁለት የቴሌቪዥን ጣቢያዎችን እና የተባበሩት ዓረብ ኤምሬትስ ንብረት የሆነ ስካይ ኒውስ የተባለ የዜና ማሰራጫን ነው፡፡
እርምጃው የተወሰደው “ለሚፈለገው የሙያ ብቃት ቁርጠኝነት እና ግልፅነት ባለመኖሩ እና ፈቃዳቸውን ባለማደሳቸው ነው" ሲል የሱዳን ዜና አገልግሎት፣ ሱና ዘግቧል።
የሱዳን ጋዜጠኞች ቡድን በበኩሉ፣ የሚኒስቴሩ እርምጃ የፕሬስ ነጻነትን የጣሰ ነው ሲል ተችቶታል፡፡
"የሳተላይት ቻናሎችን መዝጋት እና በሙያው የሚሰሩትን መገደብ ሙያዊ ሥነምግባር የጠበቁ ሚዲያዎችን ድምጽ ከማጥፋት በተጨማሪ አሉባልታ እና የጥላቻ ንግግሮች እንዲስፋፉ በር ይከፍታል"ሲል ቡድኑ ማክሰኞ በላከው መግለጫ አስታውቋል።
ሱዳን ለጋዜጠኞች ፈታኝ ሁኔታ ውስጥ ትገኛለች። እ.ኤ.አ. በ2023 የፕሬስ ነፃነትን ሁኔታ የሚከታተለው ድንበር የለሽ የጋዜጠኞች ቡድን፣ ሱዳንን በመገናኛ ብዙሃን ነፃነት ከ180 ሀገራት 148 ደረጃ ላይ አስቀምጧታል።
በሁለቱ የሱዳን ጀኔራሎች መካከል የተፈጠረው ግጭት ጋዜጠኞች ለገጠማቸው ብርቱ ፈተና አስተዋጽኦ ማድረጉንም የመገናኛ ብዙሃንና የፕሬስ ነጻነት ቡድኖች አስታውቀዋል።