በሱዳኑ አመጽ ሁለት ሰዎች ተገደሉ

እኤአ ሰኔ 30 2019 በሱዳን የተደረገው ተቃውሞ

ትናንት ምሽት ካርቱም ውስጥ የሱዳንን አብዮት ሁለተኛ ዓመት ምክንያት በማድረግ በተቀሰቀሰ ተቃውሞ የሱዳን ወታደሮች ከተቃዋሚዎቹ ወገን 2 ሰዎችን ገድለው 16 የሚሆኑትን ደግሞ አቁሰለዋል፡፡ የሱዳን ባለሙያዎች ማህበር ጥቃቱን ያወገዘ ሲሆን ጥቃቱ በመሰብሰብ ነጻነት ላይ የተቃጣ ነው ብሎታል፡፡ የሱዳን ጠቅላይ ሚኒስትር አቡድላ ሀምዶክ ጠቅላይ አቃቢ ህጉ ስለ ሁኔታው በአስቸኳይ ማጣራት እንዲጀምሩ አዘዋል፡፡የቪኦኤ ዘጋቢ ማይክ አቲት ከሱዳን ካርቱም የላከውን ዘገባ ደረጀ ደስታ ያቀርበዋል፡፡

የሱዳን ህክምና ባለሙያዎች ማህበር፣ ለተቃውሞ የወጡ ሁለቱ ሰዎች፣ በሱዳን መከላከያ ሚኒስቴር ዋና ጽ/ቤት ፊት ለፊት የተገደሉ መሆናቸውን አረጋግጠዋል፡፡

የማህበሩ አባል ዶ/ር ዋልዲን አል ፈቂ፣ ሱዳን ኢን ፎከስ ለተባለው ሚዲያ በሰጡት መግለጫ፣ 37 ሰዎች የቆሰሉ መሆናቸውን ገልጸው ፣ህክምና ላይ መሆናቸውንም ተናግረዋል፡፡

“አምስት የሚሆኑት በጽኑ የቆሰሉ ሲሆን ካርቱም አቅራቢያ ወደ ሚገኝ ሆስፒታል ተወስደዋል” ያሉት አልፋቂ፣ አንዳንዶቹም ከትራፊክ ከግጭቱ ቦታ ሲሸሹ በትራፊክ አደጋ የተጎዱ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

አያይዘውም “የሽግግር መንግስቱ ፍትህ መስፈኑን የማረጋገጥ ኃላፊነት ያለበት ሲሆን፣ ችግሩን የፈጠሩትም ሰዎች ተጠያቂ መሆን አለባቸው፡፡ ያ ካልሆነ ግን በመንግስት ላይ የተቀሰቀሰው ተቃውሞ ያይላል” ብለዋል፡፡

ሰኻር አል ጀዙሊ፣ የአቡ አዳም የተባለው የተቃዋሚዎች ኮሚቴ አባል ናቸው፡፡ እሳቸውም ግድያውን ያወገዙ ሲሆን፣ ችግሩ የተፈጠረው “በወታደራዊው እና በሲቪሉ መንግሥት አመራሮች መካከል ባለ ውሳኔ የመስጠት ችግር የተፈጠረ ነው” ብለዋል፡፡

Your browser doesn’t support HTML5

በሱዳኑ አመጽ ሁለት ሰዎች ተገደሉ


አለጀዙሊ ይህንኑ ለሱዳን ኢን ፎከስ ሲያስረዱ

“አሁን ያለን ህብረት በጣም የላላ እና ያካሄድነውን አብዮት የሚመጥን አይደለም፡፡ አብዮቱ ከመንግሥት የተነጠለ ሲሆን፣ አሁንም እየተካሄደ ነው፡፡ ወጣቶች እንደገና ለተቃውሞ ጎዳና ላይ እየወጡ ሲሆን ጨርሶም አልተገበሩም፡፡ አሁን ያለን ትብብርና ህብረት ግን የነሱን መብት ያስከበረ አይደለም፡፡” ብለዋል፡፡

ሌላኛው አህመድ የሱፍ ሲሆኑ የኡማ ብሄራዊ ፓርቲ አባል ናቸው፡፡ አሁን ያለው ህገመንግሥት ለወታደራዊው መንግስት የሚያደላ ነው በማለት፣ የፍትህ ኮሚቴ እንዲቋቋም ጥሪ ያቀርባሉ፡፡ የሱፍ ለሳውዝ ሱዳን ኢንፎከስ ሲናገሩ እንዲህ ብለዋል

እነዚህ ጥሩ አጋጣሚዎች አይደሉም፡፡ እጅግ በጣም ወደ ኋላ ይወስዱናል፡፡ እንዲህ ያሉ ወንጀሎች ጨርሶ እንዲያበቁ በጣም አስፈላጊ የሆነውን የፍትህ ሽግግር ወይም ኮሚሽን ማቋቋም ይኖርብናል፡፡ አገራችን አሁን እጅግ አደገኛ በሆነ አቅጣጫ ላይ ስትሆን ከገደሉ ጫፍ ላይ ተንጠልጥላ ትገኛለች፡፡” ብለዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ኻምዶክ፣ የመከላከያ ሚኒስትሩን፣ ጠቅላይ አቃቢ ህጉንና የደህንነቱና ዋና ድሬክተር ጨምሮ፣ ከከፍተኛ ባለሥልጣናትን በመጥራት አስቸኳይ ስብሰባ አድርገዋል፡፡ ሁኔታው በአስችኳይ እንዲጣራም መመሪያ ሰጥተዋል፡፡ ባስለሥልጣናቱ ሁከቱን የፈጠሩትና ለጥቃቱ ምክንያት የሆኑት ሰዎች ያለምንም መዘግየት ለፍርድ እንዲቀርቡ ተስማምተዋል፡፡

እኤአ በ2019 የጸጥታ ኃይሎች፣ በሱዳን ጦር ሠራዊት ዋና መ/ቤት ፊት ለፊት የመቀመጥ አድማ አድርገው የነበሩ ሰላማዊ ተቃዋሚዎችን በመውረር 127 ሰዎች መግደላቸውን የሱዳን ተቃዋሚዎች ይናገራሉ፡፡ ባለሥልጣናቱ ግን የሞቱት ሰዎች 87 ብቻ ናቸው ይላሉ፡፡ ምንም እንኳ ለረጅም ጊዜ ምርመራ የተካሄደበት ቢሆንም እስካሁን በግድያው ተጠያቂ የሆነ ወገን አልተገኘም፡፡

ከፍተኛ ባለሥልጣናቱ ስብሰባቸውን ተከትሎ ወዲያውኑ ባወጡት መግለጫቸው “የዛሬ ሁለት ዓመት በመከላከያ ሚኒስትር ዋናው ጽ/ቤት ፊት ለፊት በተፈጠረውና ወንድና ሴቶች ልጆቻችን ህይወታቸው ያጡበት ሁኔታ ዛሬም ድረስ ከውስጣችን ያልወጣና የሱዳንን ቤተሰቦች ልብ የሰበረ መሆኑን ይታወሳል፡፡” ብለዋል፡፡