በሱዳን ከመደበኛ ሠራዊቱ ጋር በመፋለም ላይ ያለው የፈጥኖ ደራሽ ኃይል በሃገሪቱ ደቡብ ምሥራቅ ክፍል በከፈተው ጥቃት ቢያንስ 80 የሚሆኑ ሰዎች መገደላቸውን የሆስፒታል ምንጮች አስታውቀዋል።
ትላንት የተፈጸመው ጥቃት የመጣው በሁለቱ ተፋላሚ ጀኔራሎች መካከል ያለው ጦርነት እልባት እንዲያገኝ ስዊዘርላንድ ውስጥ ጥረት በመደረግ ላይ ባለበት ወቅት ነው።
ትላንት በርካታ አስከሬኖችንና የተጎዱ ሰዎችን መቀበላቸውንና የሟቾቹ ቁጥርም 80 እንደደረሰ ጃልጊኒ በተሰኘው የሕክምና ማዕከል የሚገኙ ምንጭ ለኤኤፍፒ ዜና ወኪል ተናግረዋል።
ኃይሎቹ ትላንት ጠዋት ጥቃት ሲከፍቱ የአካባቢው ሰዎች ለመመከት ሞክረው የነበረ ሲሆን፣ ኃይላቸውን አጠናክረው በመመለስ ቤቶችን አቃጥለው ግድያ መፈጸማቸውን፣ ዛሬ ዓርብም አስከሬኖች በመንገድ ላይ እንደሚገኙ አንድ ከጥቃቱ የተረፉ ግለሰብ ለዜና አገልግሎቱ አስታውቀዋል።
የፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ ባለፈው ሰኔ ሴናር የተባለች ስፍራ መቆጣጠሩን ተከትሎ 726 ሺሕ የሚሆኑ ሰዎች አካባቢውን ጥለው ተሰደዋል።