ዋሺንግተን ዲሲ —
የሱዳን የሽግግር መንግሥት የቀድሞውን የሀገሪቱ ፕሬዚዳንት ኦመር አል ባሽርን ለዓለምቀፍ የወንጀል ችሎት ለማስረከብ ተስማምቷል።
ዛሬ ስለ ውሳኔው ወሪ የተሰማው የሱዳን መንግሥትና የዳርፉር ክልል አማጽያን በደቡብ ሱዳን መዲና ተገናኝተው ከተነጋገሩ በኋላ ነው ተብሏል።
የፍትህና የእኩልነት ንቅናቄ የተባለው የአማጽያን ድርጅት ተወካይ አሕመድ ቱጉድ ለአሜሪካ ድምፅ በተናገሩት መሰረት ባሽር የሚገኙባቸው አራት በዓለምቀፍ የወንጀል ችሎት የተከሰሱ ሱዳናውያን ሄግ ለሚገኝው የዓለምቀፍ የወንጀል ችሎት እንዲሰጡ ሁለቱም ወገኖች ተስማምተዋል።
ሱዳን ውስጥ በመዋጋት ላይ ያሉት ወገኖች ሁሉ ሙሉ የሰላም ሥምምነት እስከሚደረጉበት ጊዜ ድረስ ተከሳሾቹን ለዓለምቀፍ ችሎት የማስረከቡ ሥምምነት ተግባራዊ እንደማይሆን ቱጉድ ጠቁመዋል። የሰላሙ ሥምምነት በቀጣዮቹ ጥቂት ሳምንታት ውስጥ ይጠናቀቃል ተብሎ እንደሚጠበቅ አክለው ገልፀዋል።