ሱዳን ከኢጋድ ጋር ያላትን ግንኙነት አቋረጠች

ፎቶ ፋይል፦ የሱዳኑ ጦር ጠቅላይ አዛዥ ጀኔራል አብደል ፋታህ አል ቡርሃን

ከሃገሪቱ ብሔራዊ ጦር ሰራዊት ጋር የተሳሰረው የሱዳን መንግሥት የተፋላሚውን የፈጥኖ ደራሽ ኃይሉን አዛዥ በጉባኤው እንዲሳተፉ በመጋበዝ ‘የሃገሪቱን ሉላዊነት ጥሷል’ ሲል ከወነጀለው የምሥራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግሥታት - ኢጋድ ጋር ያለውን ግንኙነት በዛሬው ዕለት ማቋረጡን አስታወቀ።

የሱዳኑ ብሔራዊ ጦር ዘጠኝ ወራት ባስቆጠረው ውጊያ ይዞታውን እያጣ በመጣበት ባሁኑ ወቅት የፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ መሪ ሞሃመድ ሃምዳን ዳጋሎ በተለያዩ የአፍሪካ አገሮች ጉብኝት ላይ መሆናቸው ተዘግቧል።

የዲፕሎማሲ ተቀባይነት ከፍ ለማድረግ የታለመ ነው በተባለ እርምጃ ኢጋድ ከነገ በስቲያ ሃሙስ ኡጋንዳ ላይ ወደሚካሄደው የመሪዎች ጉባኤ ዳጋሎን ጋብዟል። ዳጋሎም ግብዣውን መቀበላቸው አስታውቀዋል።

ይሁንና እርምጃው የጦር ሰሠራዊቱ ዋና አዛዥ እና የሃገሪቱ መሪ አብዱልፈታህ አል ቡርሃን ታማኝ የሆኑትን የሱዳኑ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አገራቸው ከህብረቱ ጋር ያላትን ግንኙነት ማቋረጧን ይፋ እንዲያደርጉ ምክኒያት ሆኗል። "የሱዳንን ሉዓላዊነት በመጣስ ወደፊት ብርቱ ችግር የሚደቅን አደገኛ ድርጊት ፈጽሟል" ሲሉም ኢጋድን ወንጅለዋል።

በሌላ በኩል ኢጋድ ካሁን ቀደም ከዩናይትድ ስቴትስ እና ከሳዑዲ አረቢያ ጋር በመሆን በተደጋጋሚ ሁለቱን ተፋላሚ የጦር ጀነራሎች ለማደራደር ጥረት ቢያደርግም ሊሳካ መቅረቱ ይታወሳል።