በሱዳን የፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ አንድ ገበያን በከባድ መሣሪያ ደበደበ

ፎቶ ፋይል፦ በግጭት ሳቢያ የቃጠሎ ጭስ ይታያል፤ ካርቱም፣ ሱዳን

በሱዳን የፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ ኤል ፋሸር በተሰኘች ከተማ በሚገኝ አንድ ገበያ ላይ ትላንት ምሽት ባደረሰው የከባድ መሣሪያ ጥቃት 18 ሰዎች መሞታቸው ተነግሯል። በደርዘን የሚቆጠሩ እንደተጎዱም የሕክምና ምንጮችን የጠቀሰው የኤኤፍፒ ዘገባ አመልክቷል።

ለ17 ወራት በዘለቀው ጦርነት የፈጥኖ ደራሽ ኃይሉና መደበኛው የሱዳን ሠራዊት የሰሜን ዳርፉር መዲና የሆነችውን ኤል ፋሸርን ለመቆጣጠር ሲፋለሙ ቆይተዋል።

በሱዳን እየተካሄደ ያለው ጦርነት፣ በተለይም በ ኤል ፋሸር የሚካሄደው ውጊያ፣ በኒው ዮርኩ የተመድ ጠቅላላ ጉባኤ ላይ መነጋገሪያ ጉዳይ ነበር።

“በኤል ፋሸር፣ ካርቱም እና ሌሎችም አስጊ ሥፍራዎች ላይ ለሚገኙ ሰዎች የሰብዓዊ ርዳታ ለማድረስ እንዲቻል ሁለቱ ተፋላሚ ወገኖች ተኩስ እንዲያቆሙ ጫና ማድረግ አለብን” ሲሉ በተመድ የአሜሪካ አምባሳደር ሊንዳ ቶማስ ግሪን ፊልድ ከትላንት በስቲያ ተናግረው ነበር።

የፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ ካለፈው ግንቦት ጀምሮ ኤል ፋሸርን ከቦ የሚገኝ ሲሆን፣ ሁለት ሚሊዮን ሰዎች በሚገኙባት ከተማ አቅራቢያ ባለው የስደተኞች ጣቢያ ረሃብ መግባቱም ታውጇል።