የኢትዮጵያ ወታደሮች የድንበሬን ወሰን ተሻግረው ገብተዋል ስትል፣ ሱዳን፣ በዚህ ሳምንት ኢትዮጵያን ከሳለች፡፡
የሱዳን የውጭ ጉዳይ ሚንስቴር ዛሬ ባወጣው መግለጫ ደግሞ፣ በኢትዮጵያና በሱዳን መካከል የተፈጠረው የድንበር ውዝግብ በመካረሩና ኢትዮጵያ በአባይ ወንዝ ላይ በምታስገነባው ግድብ ዙሪያ ያለው ሁኔታ ለመምከር ሱዳን በኢትዮጵያ የሚገኘው አምባሳደሯን መጥራቷን አስታውቋል፡፡
የዛሬው የሱዳን ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መግለጫ የወጣው፣ በሁለቱ ጎረቤት አገሮች መካከል የመሬት ይገባኛል ውዝግብ ባለበት ሁኔታ ውስጥ ነው፡፡
የድንበር ውዝግቡ፣ ግብጽና ሱዳን “የተፈጥሮ ውሃ አቅርቦታችንን አደጋ ላይ ሊጥል ይችላል” በሚል ፣ኢትዮጵያ በአባይ ወንዝ ላይ በምትገነባው ግዙፍ የኃይል ማመንጫ ግድብ ዙሪያ፣ በሚያነሱት ክርክር ላይ፣ ሌላ ተጨማሪ ጫና ፈጥሯል፡፡
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ቃል አቀባይ መንሱር ቡላድ አብደላ፣ ለፈረንሳዩ የዜና ወኪል እንደተናገሩት፣ ሱዳን በሁለቱ አገሮች ግንኙነት ዙሪያ ለመምከር በኢትዮጵያ የሚገኙት አባሳደሯን ወደ ካርቱም ጠርታለች፡፡ የውይይቱን ምንነት በዝርዝር ባያብራሩም ምክክሩ እንደተጠናቀቀ መልዕክተኛው አምባሳደር ወደ ሥራቸው ቦታ እንደሚመለሱ አስታውቀዋል፡፡
Your browser doesn’t support HTML5
በዚህ ሳምንት የሱዳን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ባወጣው መግለጫ ደግሞ ኢትዮጵያ ንቀት በተሞላበት ሁኔታ በሱዳን መሬት ላይ ወረራ ፈጽማለች ብሏል፡፡
መግለጫው የኢትዮጵያ ወታደሮች በሰሜን ምዕራብ ኢትዮጵያና በምስራቅ ሱዳን ድንበር አቅራቢያ አልፋሽጋ አካባቢ የሚገኘውን ድንበር አቋርጠው ገብተዋል በማለት ከሷል፡፡
የኢትዮጵያ መንግሥት ባለፈው ወር ባወጣው መግለጫ፣ ሱዳን የኢትዮጵያን ድንበር ዘልቃ መግባቷን አስታውቋል፡፡ ሱዳን ድንበር እያቋረጠች የምትፈጽመውን ወራራም ማቆም አለባት ሲልም ጥሪውን አቅርቧል፡፡
ከሱዳን የተገኘው ዘገባ እንደሚያሳየው በአልፋሽጋ አካባቢ ያለው ውዝግብ የ50 ዓመታት ታሪክ አለው፡፡ ይሁን እንጂ እንደገና የተቀሰቀሰው በኢትዮጵያ ትግራይ ክልል የተነሳውን ጦርነት በመሸሽ በአስርሺዎች የሚቆጠሩ ስደተኞች በምስራቅ በኩል ድንበሩን አቋርጠው ወደ ሱዳን መግባት ከጀመሩበት ጊዜ አንስቶ ነው፡፡
ባፈው ጥር ወርም እንዲሁ ሱዳን የኢትዮጵያ ጦር አውሮፕላን የሱዳንን የአየር ክልል ጥሶ በሯል ስትል ኢትዮጵያን የከሰሰች ሲሆን፣ ኢትዮጵያ ደግሞ የሱዳን ወታደሮች ድንበር ጥሰው በመግባት በኢትዮጵያ ዜጎች ላይ ዝርፊያ ፈጽመዋል ስትል ክሷን አሰምታለች፡፡
በኳታር የሚኖሩት የሱዳን ፖለቲካ ተንታኝ ሞሀመድ አህመድ እንደሚሉት ከሆነ ኢትዮጵያም ሆነች ሱዳን የትክክለኛውን ጦርነት ዋጋ መሸከም የሚችሉ አይደሉም ይላሉ፡ ይህን ሲያስረዱም
“በኢትዮጵያና በሱዳን ያሉት ውሳኔ ሰጭዎች ወደጦርነት ማምራት የማይረባ ነገር መሆኑን ያውቃሉ፡፡ በኢትዮጵያ የኢኮኖሚ ልማት ያለ ሲሆን በሱዳንም የዴሞክራሲ ለውጥ አለ፡፡ ማንኛውም ጦርነት በሁለቱም አገሮች የተገኘውን ውጤት አደጋ ላይ ይጥላል፡፡ ይሁን እንጂ ግን መሪዎቹ በአገር ውስጥ ያሉ ግጭቶችን ለማርገብ ጠላት እያፈላለጉ ነው፡፡”
የድንበሩ ውዝግብ ኢትዮጵያ በአባይ ወንዝ በምትገነባው የኃይል ማመንጫ ግድብ በተነሳው አለመግባባት ላይ ተጫማሪ ውጥረት ይፈጥራል፡፡ ሱዳንና ግብጽ ግድቡ ከወንዙ የሚያገኙትን ተፈጥሯዊ የውሃ አቅርቦታቸውን እንዲቀንስ ያደርገዋል ብለው ይሰጋሉ፡፡
በካርቱም የሚገኙት የፖለቲካ ተንታኝ አልታፊ ሞሀመድ ከውጥረቱ ጀርባ ያለው ዋነኛው ምክን ያት ግድቡ ነው በማለት እንዲህ ይላሉ
“የውዝግቡ ሁሉ ምክንያት የህዳሴው ግድብ ነው፡፡ ያ አለመግባባትና ውዝግብ ምንም እንኳ በጦርነት የማይገባደድ ቢሆንም ሁለቱንም ወገኖች በጠረጴዛ ዙሪያ አብረው ተቀምጠው እንዲነጋገሩ ሊያስገድዳቸው ይችላል፡፡"
ሱዳንና ኢትዮጵያ በድንበር ውዝግቡ ላይ ለመነጋገር በደቡብ ሱዳን የቀረበውን ሽምልግልና እንደሚቀበሉ አስታውቀዋል፡፡ ይሁን እንጂ ግን ኢትዮጵያ ድርድሩ ከመጀመሩ በፊት ሱዳን ከያዘቻቸው የኢትዮጵያ መሬቶች በአስቸኳይ ለቃ እንድትወጣ ጠይቃለች፡፡
(የቪኦኤ ዘጋቢ ናባ ሞሃዲን ከካርቱም ከላከችውንና ከፈረንሳይ የዜና ወኪል ዘገባን የተጠናቀረ)