በሱዳን ቀይ ባህር ጠረፍ ላይ የምትገኘው ፖርት ሱዳን ለኮሌራ ወረርሽኝ ተጋልጣለች፡፡
ወረረሽኙ የተባባሰው በርስ በርስ ጦርነት ውስጥ በምትገኘው የሰሜን ምስራቅ አፍሪካዊቷ ሀገር ሱዳን፣ የህክምና እጥረት እየተባባሰ በመምጣቱ እንደሆነ ተመልክቷል፡፡
በግጭቱ ለተፈናቀሉ ሰዎች ወደ መጠለያነት በተቀየረው የአካባቢው ዩኒቨርስቲ መኝታ ቤቶች ውስጥ ቢያንስ 1,000 ሰዎች እንደሚገኙ የተገለጸ ሲሆን ከሁለት ሴት ልጆቿ መካከል አንዷን በኮሌራ ወረርሽኝ ያጣችው ተፈናቃይዋ ጁሊያ አደም ትልቅ ፍርሃት ውስጥ መሆናቸውን ተናግራለች፡፡
ተፋናቃዮቹ ባሉበት ስፍራ ባሉ የንጽህና ጉድለቶች የተነሳ ወረርሽኙ ከፍተኛ ስጋት የፈጠረ መሆኑን ጁሊያ ገልጻለች፡፡
ጁሊያና ልጆቿ በሱዳን ለስምንት ወራት በዘለቀው የእርስ በርስ ጦርነት ከመኖሪያ ቤታቸው ከተፈናቀሉ ከ7 ሚሊዮን በላይ ሰዎች መካከል እንደሚገኙ ተገልጿል፡፡
በሱዳን በሁለቱ ወታደራዊ አዛዦች በጀኔራል አብደል ፋታህ ቡርሃን እና የፈጠኖ ደራሹ መሪ ጀኔራል መሃመድ ሃምዳን ደጋሎ መካከል በተፈጠረ አለመግባባት በሀገሪቱ ለወራት የዘለቀ የርስ በርስ ጦርነት እየተካሄደ መሆኑ ይታወቃል፡፡