በዚምባብዌ ሸማቾች ከሱቅ ይልቅ የጎዳና ላይ ግብይትን ይመርጣሉ

በዚምባብዌ ሸማቾች ከሱቅ ይልቅ የመንገድ ላይ ነጋዴዎችን ይመርጣሉ

በዚምባብዌ ሸማቾች ከሱቅ ይልቅ የመንገድ ላይ ነጋዴዎችን ይመርጣሉ

የዚምባቡዌ ገበያተኞች፣ አስቤዛቸውን ከሱቆች ከመግብየት ይልቅ፣ ከጎዳና ላይ ነጋዴዎች በመሸመት ላይ ናቸው። ምክንያቱ ደግሞ፣ የአገሪቱ ገንዘብ ከዶላር አንጻር ዋጋውን በማጣቱ እና በሱቁች የሚገኘው ሸቀጥ ደግሞ ዋጋው እጅግ በመናሩ ነው፤ ተብሏል። በመንገድ ላይ የሚሸጡት ዕቃዎች ግብይት ግን፣ በአሜሪካ ዶላር እንደሚካሔድ፣ የአሶሺዬትድ ፕረስ ዘገባ አመልክቷል።

በዚምባቡዌ፣ ሱቆች፥ ግብይቱን በአገሪቱ ገንዘብ እንዲያካሒዱ ይገድዳሉ። ሁለቱም ገንዘቦች፣ በአገሪቱ ሕጋዊ መገበያያ ናቸው። የጎዳና ላይ ነጋዴዎቹ፣ በዶላር መገበያየትን ሲመርጡ፤ በሱቆቹ ያለው ሸቀጥ ዋጋ በየቀኑ እያሻቀበ በመምጣቱ ምክንያት፣ ሸማቾች በጎዳና ላይ ወደሚሸጡትና ዋጋቸው ወደተረጋጋው ሸቀጦች አተኩረዋል።

በመንገድ ላይ የሚገኙት ነጋዴዎች ፉክክርም፣ ሸማቾቹ ወደ እነርሱ እንዲሳቡ አድርጓል። ከምግብ ሸቀጥ እስከ መኪና መለዋወጫ ድረስ ለግብይት የዘረጉት ነጋዴዎቹ፣ ለሸማቾች በነፃ የሚሰጡት ተጨማሪ ዕቃ ሳቢ ነው፤ ተብሏል።

ዚምባቡዌ ለአንድ ዓመት በዘለቀ የገንዘብ ቀውስ ውስጥ ከቆየች በኋላ፣ እ.አ.አ. በ2009፣ በዓለም አስተማማኝ የኾነውን ዶላር ተጨማሪ መገበያያ እንዲኾን ወስናለች፡፡የጎዳና ላይ ግብይቱ በዶላር በመኾኑ፣ ዋጋው መረጋጋቱን የአሶስዬትድ ፕረስ ዘገባ አመልክቷል።