ዩናይትድ ስቴትስ በኢትዮትጵያና በኤርትራ መካከል የተፈረመውን የሰላም ስምምነት እንደምታደንቅ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሯ ማይክ ፖምፔዮ አስታወቁ።
የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤቱ ቃል አቀባይ ቢሮ ዛሬ ባወጣውና ባሠራጨው መግለጫ “ሃገረ ኤርትራና የኢትዮጵያ ፌደራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ ሐምሌ 1/2010 ዓ.ም. ለሰላምና ለፀጥታ ያሳዩትን ቁርጠኛነት በደስታ ትቀበላለች” ሲሉ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ያስተላለፉትን መልዕክት አስፍሯል።
ይህ የኢትዮጵያና የኤርትራ የጋራ መግለጫ ለሃያ ዓመታት የዘለቀውን ግጭት በተሣካ ሁኔታ እንዲያበቃ ማድረጉንም የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ፖምፔዮ አመልክተዋል።
ሚኒስትሩ አክለውም “የኢትዮጵያው ጠቅላይ ሚኒስትር አብይና የኤርትራው ፕሬዚዳንት ኢሣያስ ዜጎቻቸውን ወደ ሰላም፣ ብልፅግናና የፖለቲካ ለውጦች ለመምራት ላሳዩት ድፍረት የተመላው እርምጃ አድናቆታችንን እንገልፃለን” ብለዋል።
በኤርትራና በኢትዮጵያ መካከል ያለውን ግንኙነት ወደ መደበኛው የተረጋጋ ሁኔታ ለመመለስ የሰላምና የወዳጅነት ሰነድ ተፈርሞ መውጣቱ የሁለቱ ሃገሮች ሕዝቦች በሚጋሯቸው የጠበቀ የፖለቲካ፣ የምጣኔ ኃብትና ማኅበራዊ ትስስሮች ላይ ይበልጥ እንዲያተኩሩ ዕድል እንደሚሰጣቸው ሚስተር ፖምፔዮ እምነታቸውን ገልፀዋል።
ዩናይትድ ስቴትስ ሂደቱን ለመደገፍ ዝግጁ መሆኗን ያስታወቀው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ መልዕክት ሁሉም ወገኖች በመጭ ቀናት በግልፅነትና በእምነት እንዲሠሩ ሃገራቸው እንደምታበረታታ አመልክተዋል።
በኢትዮጵያና በኤርትራ መካከል ሰላም መስፈኑ በአፍሪካ ቀንድና በቀይ ባህር አካባቢ እንዲኖር የሚፈለገውን ለመረጋጋት፣ ለፀጥታና ለልማት የመጣር ተግባር ይበልጥ ያቀላጥፈዋል” ብለዋል የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ፖምፔዮ።