ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን “ባለፈው ዓመት ኮቪድ ለያይቶን ነበር። ዛሬ ከሁሉም በላይ እንደ አሜሪካ በአምባገንነት ላይ ነፃነትን ለማወጅ ዴሞክራቶች፣ ሪፖብሊካንና ነፃዎች ተገናኝተናል። ሲሉ የመጀመሪያውን የሃገሪቱን ሁኔታ ንግግራቸውን ጀምረዋል።
ፕሬዚዳንት ባይደን የሩሲያውን ቭላዲሚር ፑቲንንና ኮቪድ-19ኝን ነፃነት ነሺዎች ሲሉ አመሳስለዋቸዋል።
ፕሬዚዳንት ፑቲን ከ6 ቀናት በፊት የጀመሩትን ጦርነት በተሳሳተ ሁኔታ አሰሉት፤ ከዩክሬን ህዝብ ጋር ተጋፈጡ።
“ብርሃን በጨለማ ላይ ይነግሣል” ብለዋል ፕሬዚዳንቱ።
በዋሺንግተን የዩክሬን አምባሳደር በአዳራሹ ተገኝተዋል። ፕሬዚዳንቱ አምባሳደሯን እንዲቆሙ ጠይቀው በእንደራሴዎቹ አስጨብጭበውላቸዋል።
“እኛ ዩናይትድ ስቴትስ ከዩክሬን ህዝብ ጋር እንቆማለን” ብለዋል ፕሬዚዳንቱ።
ኔቶ የተቋቋመው ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት በኋላ በአውሮፓ ሰላምና መረጋጋት ለማስጠበቅ እንደነበረ ፕሬዚዳንት ባይደን አስታውሰው “አውሮፖ መልስ የሚሰጥ ያልመሰላቸው ፑቲን ተሳስተዋል” ብለዋል። ፑቲንን ለመጋፈጥ “ከአውሮፓ አጋሮቻችን ጋር ከምንጊዜም በላይ አንድ ሆነናል” ብለዋል። “የአውሮፓ ህብረት 27 አባል ሃገሮችና እንግሊዝና አውስትራሊያን ጨምሮ በፑቲን ላይ ከባድ ህመም ጥለዋል” ብለዋል። በሩሲያ ላይ እጅግ የበረታ የምጣኔ ኃብት ማዕቀብ በመጣል እንደሚቀጥሉ ተናግረዋል። “ሩስያ ላይ 600 ቢሊዩን ዶላር ዋጋ እንዲያጣ አድርገናል፤ ቴክኖሎጂን እንዳይጠቀሙ አድርገናል” ብለዋል።
የአሜሪካ የአየር ክልል ሁሉ ለማንኛውም የሩሲያ በረራ ዝግ መሆኑን አውጀዋል። ሩብል በ30 ከመቶ፣ የሩሲያ የሸቀጥ ገበያ በ40 ከመቶ ማሽቆልቆሉን ተናግረዋል። ለዩክሬን የአንድ ቢሊዮን ዶላር እርዳታ እንደሚስጡና ሰብዓዊ ድጋፍ በመስጠት እንደሚቀጥሉ አስታውቀዋል።
የጦር ኃይሎቻቸው ዩክሬን ውስጥ እንደማይዋጉ፤ የኔቶን ግዛት ሁሉ ግን እያንዳንዷን ነቁጥ መሬት በሙሉ ኃይሎቻቸው እንደሚጠብቁ አስታውቀው፣ የጦር ኃይሎቻቸውን ሁሉ በተጠንቀቅ ማቆማቸውን አስታውቀዋል። ማዕቀቦቹ ሁሉ የሩሲያ ምጣኔ ኃብት ላይ እንዲያነጣጥሩ በዓለም ዙሪያ 60 ቢሊዮን በርሜል የመጠባበቂያ ነዳጅ እንዲሁም አሜሪካ 30 ሚሊዮን በርሜል እንደምታንቀሳቀስ ተናግረዋል። “ፑቲን የነፃውን ዓለም ጥንካሬ አያላሉትም” ብለዋል - ፕሬዚዳንት ባይደን።
ፕሬዚዳንት ባይደን ንግግራቸውን ወደ ኮቪድ-19 አዙረው በአሜሪካዊያን ላይ ያደረሰውን ጉዳት አብራርተዋል። ለአሥሮች ሚሊዮኖች አሜሪካዊያን ቤተሰቦች ድጋፍ ማድረጋቸውን ተናግረዋል። የአሜሪካ መድህን ዕቅድ ሠራተኛ አሜሪካዊያንን እንደሚረዳና መሥራቱንም ገልፀዋል።
6.5 ሚሊዮን ሥራ ባለፈው ዓመት ብቻ መፈጠሩን ተናግረዋል። በአንድ ዓመት ውስጥ እንዲህ ዓይነት ለውጥ ታይቶ አያውቅም ብለዋል። ምጣኔ ኃብቱ በ5.7 ከመቶ ማደጉን ገልፀዋል። ይህ ባለፉት አርባ ዓመታት ታይቶ አይታወቅም። ባለመካከለኛ ገቢ አሜሪካዊያንን ማሳደግና ማጠናከር፣ አሜሪካን መልሶ መገንባት መሆኑን ተናግረዋል።
የሃገሪቱን መሠረተ-ልማት መልሶ መገንባት እንደሚያስፈልግ ፕሬዚዳንት ባይደን አስታውቀዋል። 500 ሺህ የኤሌክትሪክ መኪኖች ቻርጅ ማድረጊያ፤ ለሁሉም ውኃ፣ ለሁሉም አሜሪካዊያን ኢንተርኔት እንደሚያቀርቡ፤ ከ65 ሺህ ማይል በላይ መንገድና 1560 ድልድዮች እንደሚገነቡ ተናግረዋል።
“የአሜሪካ ምርቶችን ግዙ፤ የአሜሪካ ሥራዎችን ደግፉ” ብለዋል። የአሜሪካ ሁሉም ግንባታዋና አገልግሎቶቿ ከአሜሪካ በተገዙ ጥሬ ዕቃዎች እንዲሆን ጠይቀዋል።
በተለያዩ የመሠረተ ልማት መስኮች ሃገራቸውን ለማጠናከር የሚችሉ ህግጋትን እንደራሴዎቹ እንዲልኩላቸው ጠይቀዋል።
ኢንቴል መዋዕለ ነዋዩን ከሃያ ቢሊየን ወደ መቶ ቢልየን ማሳደጉን፣ ለኤሌክትሪክ መኪኖች ፎርድ ኩባንያ 11 ቢልዮን ዶላር፣ ጂ ኤም 7 ሚሊየን ዶላር በተጨማሪ መመደባቸውን አድንቀዋል።
350 ሺህ አዳዲስ አምራች ሥራዎች ባለፈው ዓመት መፈጠራቸውን ፕሬዚዳንቱ አመልክተው ምጣኔ ሃብቱ ማንም ከገመተው በፈጠነ ሁኔታ እያደገ መሆኑን ተናግረዋል። ሃገሪቱ ያለባትን ግሽበት ለመቀነስ ወጭን መቀነስና የተሻሉና ለአቅም ተመጣጣኝ የሆኑ ምርቶች አሜሪካ ውስጥ መመረት እንዳለባቸው ተናግረዋል። የተሻለች አሜሪካን እንገንባ ብለዋል ባይደን። አሜሪካዊያን ለመድኃኒት ከማንም በላይ እንደሚከፍሉ ተናግረው በሃኪም የሚታዘዙ መድሃኒቶች ዋጋ መቀነስ እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል።
ሜዲኬር የሚባለው የመንግሥት የጤና መድህን የመድሃኒት ዋጋ መደራደር እንዲችል ሃሳብ አቅርበዋል። ቤተሰቦች ያለባቸውን የኢነርጂ ዋጋ መቀነስ አስፈላጊ መሆኑን ተናግረዋል። ለዚህም ታዳሽ ኢነርጂን ማስፋፋት፣ የህፃናት ደህንነት ጥበቃ ወጭን መቀነስ እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል። ዕቅዳቸው የህፃናት ወጭን በግማሽ መቀነስ መሆኑን አስታውቀዋል። እናቶች ህፃናትን ማሳደጊያና መንከባከቢያ ወጭ፣ እንዲሁም በቤት ዋጋ መናር ምክንያት እናቶች ብዙ እንደሚንገላቱ አመልክተዋል።
ማንም ከ400 ሺህ ዶላር በታች የሚያገኝ የታክስ ጭማሪ እንደማይደረግበት አስታውቀዋል። የታክስ ህጉ ፍትሃዊ እንዳልሆነ፤ ከበርቴዎችም የሚገባቸውን እንዲከፍሉ እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል።
ባለፈው ዓመት የአርባ ቢሊዮን ዶላር ትርፍ ያገኙ 55 የፎርቹን 500 ኩባንያዎች ለቀረጥ አንድ ሳንቲም እንኳ አለመክፈላቸውን ተናግረዋል። ለማዕከላዊ ባንኩ ወይም ለጠቅላይ ግምጃ ቤቱ ኃላፊነት ያጯቸውን ሰው እንዲያፀድቁላችው እንደራሴዎችን ጠይቀዋል።
“እኔ ካፒታሊስት ነኝ፤ ካፒታሊዝም ያለውድድር ካፒታሊዝም ሳይሆን ብዝበዛ ነው” ብለዋል ፕሬዚዳንት ባይደን። አሜሪካዊያን ሸማቾችን ያለአግባብ የሚስከፍሉ ኩባንያዎችን እንዲሚያሳድዱ አስጠንቅቀዋል ፕሬዚዳንቱ። ምጣኔ ሃብቱን ለማጠናከር የተለያዩ ሙያዎች ሥልጠናዎች አስፈላጊ መሆናቸውንና መሠረታዊ ክፍያ በሰዓት 15 ብር እንዲሆን ጠይቀዋል። የማኅበረሰብ ኮሌጆችን ጥቅም አብራርተዋል። “በጥንካሬያችን፣ በነደፍነው ምላሽ ወደ ተሻለ ጊዜ ወጥተናል” ብለዋል።
ኮቪድ-19ኝን በመዋጋት በተገኘው አበረታች ውጤት ምክንያት የበሽታዎች መቆጣጠሪያና መከላከያ ማዕከላት /ሲዲሲ/ ሰሞኑን ባወጣው አዲስ መመሪያ ማስክ ማውለቅ እንደሚቻል መናገሩን እንደመልካም ዜና ገልፀዋል። ሰው ክትባት እንዲወስድ አበረታትተዋል። ዕድሜያቸው ከ5 ዓመት በታች ለሆኑ ህፃናት ክትባት ለመሥራት ተመራማሪዎቹ እየጣሩ መሆናቸውን ባይደን አስታውሰው ፋይዘር በዚህ ወር 1 ሚሊዮን ለህክምና የሚውሉ ፀረ-ኮሮናቫረስ ኮቪድ መድኃኒቶችን እንደሚያመርት፣ በመጭው ወር ምርቱን እጥፍ እንደሚያደርግ፤ አስተዳደራቸው ለሚያስፈልጋቸው ሁሉ ያለክፍያ እንዲደርስ እንደሚያደርግ ገልፀዋል።
ለአዳዲስ የኮሮናቫይረስ ዝርያዎች መዘጋጀት እንደሚያስፈልግም ፕሬዚዳንቱ መክረዋል።
ፌዴራል መንግሥቱ ስፋት ያለው ሠራተኛ ሥራው ላይ በአካል ተግኝቶ መሥራት እንደሚጀምር፤ ትምህርት ቤቶች ደህንነታቸው ተጠብቆ እንደሚቀጥሉ ተናግረዋል። 400 ሚሊዮን ክትባት ለ212 ሃገሮች መስጠታቸውን ተናግረዋል።
“እያንዳንዳችን በሌላችን ውስጥ ጠላት መፈለግ ሳይሆን እንደ አሜሪካዊያን ወገኖች እንተያይ” ብለዋል። በህገወጥ የመሣሪያ ዝውውር ላይ እርምጃ ለመውሰድ፤ ወንጀልን ለመቀነስ እንደራሴዎቹ እንዲያግዟቸው ጠይቀዋል።
“አሜሪካ ውስጥ መሠረታዊው መብት ድምፅ የመስጠት መብት ነው” ብለዋል። ድምፅ የመስጠት ነፃነትን ህግ እንደራሴዎቹ እንዲያፀድቁ ጠይቀዋል።
ለዩናይትድ ስቴትስ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ካታንጂ ብራውን ጃክሰን የመጀመሪያዪቱ ጥቁር ሴት ዳኛ እንዲሆኑ ማጨታቸውን ተናግረዋል። ስለድንበር ጥበቃ ሲናገሩም አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን እንደሚዘረጉ አስታውቀዋል።
“ነፃነትና መብቶችን መጠበቅ የሴቶችን መብት ከመጠበቅ ይነሳል” ብለዋል ፕሬዚዳንት ባይደን። የሴቶችን የመምረጥ መብት እናጠንክር ብለዋል። የተመሳሳይ ፆታ አፍቃሪዎችን በተመለከተ ኮንግረሱ የዕኩልነት ህግ አፅድቆ እንዲያቀርብላቸው ጠይቋል። በሁሉም ወገኖች የተደገፉ ሰማንያ ህግጋትን ባለፈው ዓመት ውስጥ መፈረማቸውን ተናግረዋል።
በአደንዛዥ ዕፆችን ወረርሽኝ ላይ ቁጥጥር እንዲበረታ፣ የእናቶች ጤና ጥበቃ ህግ እንዲፀድቅ፣ በህፃናት ላይ የተነጣጠሩ ማስታወቂያዎች እንዲቆሙ እንዲደረግ ጠይቀዋል። “የሃገራችን አከርካሪዎች ናቸው” ላሏቸው የሃገሪቱ አርበኞች እንክብካቤ እንዲጠናከርላቸው፣ አጠቃላይ የጤና ጥበቃ ዋስትና እንዲያገኙ አሳስበዋል።
“ካንሰርን ላማቆም እንደሚሠሩ ልጇቸውን በካንሰር ያጡት ፕሬዚንዳት አመልክተው የካንሰርን የሞት መጠን በሚቀጥሉት 25 ዓመታት በግማሽ ለመቀነስ እንደሚጥሩ ገልፀዋል።
“እኛ በታሪክ ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ ጠንካራ ነን፤ ዴሞክራሲን እንጠብቃለን፤ የሃገራችን ሁኔታ እጅግ ጠንካራ ነው፤ ምክንያቱም አሜሪካዊያን ጠንካሮች መሆናችን ነው።” ብለው የመጀመሪያውን ንግግራቸውን ደምድመዋል።
የአዮዋ አገረገዥ ኪም ሬይኖልድስ የሪፓብሊካኑን ምላሽ አሰምተዋል
“አሜሪካን መልሰን የተከበረች እናድርግ” ብለዋል። ፕሬዚዳንት ባይደን ጦሩን ከአፍጋኒስታን ማውጣታቸውን በብርቱ ነቅፈዋል። “ወዳጆቻችንን ከዱ” ብለዋል።
በባይደን ጊዜ ሰሜን ኮሪያ መልሳ ሚሳይሎችን መሞከር መጀመሯን አስታውሰዋል።
ዩክሬናዊያን በጥንካሬ እየተዋጉ መሆናቸውንና እንደሚደግፏቸው ተናግረዋል።
ፕሬዚዳንቱ “ከወታደራዊ ዝግጁነት ይልቅ፤ የፖለቲካ ትክክለኛነትን መርጠዋል” ብለዋል። “ጊዜው ወሣኝ የመሆን የመምራት ነው” ሲሉ አክለዋል። “ፕሬዚዳንቱና ዴሞክራቶቹ ሃገሪቱን ወደ ግሽበት ከትተዋታል፤ የነዳጅ ዋጋ አሻቅቧል” ብለዋል። “ወጭ አብዝተዋል” ብለዋል። ለመልሶ ግንባታ ዕቅዳቸው የአንድ ትሪሊዮን ዶላር ወጭ መጠየቃቸውን ተቃውመዋል። “ዋጋ እየናረ፣ ደመወዝ እየቀነሰ ነው” ብለዋል።
በኑሮ ውድነት ምክንያት የእናቶችና የአባቶች ገቢ መቀነሱን ጠቁመዋል። “አሜሪካዊያንን እንቅልፍ የሚያሳጣቸው ምን እንደሆነ ጠይቁ” ብለዋል። ዴሞክራቶች በሚቆጣጠሯቸው ካሊፎርኒያ፣ ኒው ዮርክና ኒው ጀርሲ ግዛቶች ውስጥ ቢሊየነሮች ብዙ እንዲያገኙ አድርገዋል። የራሳቸው ፓርቲ ሰዎች “ይበቃል” ብለዋቸዋል ሲሉ አገረ ገዥ ሬይኖልድስ ተችተዋል።
“ባይደን ክትባትን ግዴታ ያደረጉት በመንግሥት ሠራተኞች ላይ እንጂ ድንበር እየጣሱ በሚገቡ ህገወጦች ላይ አይደለም” ሲሉ ሬይኖልድስ ወቀሳቸውን አሰምተዋል።
“ፕሬዚዳንት ባይደን ድንበር መጠበቅ፣ የሰውና የአደንዛዥ ዕፅን ዝውውር ለመቆጣጠር ፍቃደኛ አልሆኑም” ብለዋል። ምጣኔ ኃብቱን በተመለከተ ዴሞክራቶች የትሪሊዮን ዶላር ወጭ ሲያበዙ ሪፓብሊካን በሚቆጣጠሯቸው አካባቢዎች ምጣኔ ኃብቱን እያረጋጉ መሆናቸውን፣ ሥራ አጥነትን እየቀነሱ መሆናቸውን፣ እየመሩ መሆንቸውን ተናግረዋል።
“የአሜሪካን የኢነርጂ ነፃነት ባዮ ነዳጆችን ጨምሮ ማረጋገጥ አለብን” ብለዋል ሪፓብሊካኗ አገረ ገዥ ኪም ሬይኖልድስ።
በፕሬዚዳንት ጆ ባይደን የመጀመሪያ የሃገራቸው ሁኔታ ንግግር ላይ የዴሞክራትና ሪፖብሊካን ኢትዮጵያ አሜሪካውያን ትንታኔ
Your browser doesn’t support HTML5