በኢትዮጵያ የመብቶች ጥሰቶች መፈፀማቸውን የዩናይትድ ስቴትስ መንግሥት ገለፀ

የዩናዩትድ ስቴትስ የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት

የዩናዩትድ ስቴትስ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ዛሬ ባወጣው የሃገራትን የሰብአዊ መብቶች አያያዝ በሚተነትነው እአአ የ2021 ዓመታዊ ሪፖርቱ፤ በኢትዮጵያ እና ኤርትራ መንግሥት ባለሥልጣናትና ታጣቂ ቡድኖች፣ ተፈጽመዋል ያላቸውን የሰብአዊ መብቶች ጥቃቶችን ዝርዝር አቅርቧል።

ሪፖርቱ በሰሜን ኢትዮጵያ ለአንድ ዓመት ከአምስት ወር በተካሄደው ግጭት እንዲሁም በተለያዩ የሃገሪቱ ክፍሎች በመንግሥት እና በተለያዩ ታጣቂ ቡድኖች ደረሱ ያላቸውን የመብት ጥሰቶችና ጥቃቶችን ዘርዝሯል።

ሪፖርቱ በመንግሥት አካላት ደረሱ ካላቸው መሰረታዊ የመብቶች ጥሰቶች መካከል፣ ከሕግ ውጭ በዘፈቀደ በመንግሥት የተፈጸሙ ግድያዎች፣ የሰዎችን ደብዛ ማጥፋት፣ ማሰቃየትና የጭካኔ ተግባራት፣ ክብረ ነክና ኢ - ሰብአዊ ቅጣቶች፣ ለሕይወት አስጊ በሆኑ እስርቤቶች ማሰር፣ የዘፈቀደ አያያዝና እስራትን እንዲሁም የፖለቲካ እስረኞች መኖራቸውን አስታውቋል።

በትግራይ በተካሄደው ጦርነት እንደ ህዩማን ራይትስ ዋች፣ አምነስት እና የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን የመሳሰሉ አካላት ባወጧቸው ሪፖርቶች መንግሥት በዘፈቃድ አሰቃቂ ግድያዎችን መፈፀሙን የሚያሳዩ በርካታ ሪፖርቶችን መውጣታቸውን የገለፀው ሪፖርት ፌደራል ፖሊስ የተፈፀሙ ወንጀሎችን ማጣራቱን ውጤቱ ግን ይፋ አለመደረጉን ገልጿል።

53 ገፅ ያለውና ባለፈው አንድ ዓመት ውስጥ ኢትዮጵያ ውስጥ የታየውን የሰብዓዊ መብት አያያዝ የሚያትተው የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ሪፖርት አካል፣ ከመንግሥት ውጪ ጥቃቶችንና የመብት ጥሰቶችን አድርሰዋል ያላቸውን ቡድኖችም በዝርዝር አካቷል፡፡

"ከመንግሥት ኃይሎች በተጨማሪ፣ በሰሜን ኢትዮጵያ በተካሄደው ግጭት የህወሃት ኃይሎች፣ የአማራ ክልል ሚሊሺያ እና ሌሎች ታጣቂ ቡድኖች በንፁሃን ዜጎች ላይ ግድያ፣ አስገድዶ መድፈር፣ በግዳጅ ማፈናቀል፣ ዝርፊያ እና የንብረት ማውደም ፈፅመዋል።” ይላል።

ሪፖርቱ አያይዞም “በስም ያልተገለፁ ያላቸው የጉምዝ ብሄረሰብ ሚሊሽያ ቡድኖች በቤንሻንጉል ጉምዝ በዓመቱ ውስጥ በተለያዩ ግዜያት በንፁሀን ዜጎች ላይ ግድያ ፈፅመዋል፣ በአፋር እና በሶማሌ ክልሎችም በሰሜን ምስራቅ ረጅም ግዜ በኖረ የወሰን ፀብ ምክንያት የአካባቢው ሚሊሺያ አባላት ንፁሃን ዜጎችን ገድለዋል፣ በምዕራብ፣ መካከለኛው እና ደቡብ ኦሮሚያ ውስጥም የኦሮሞ ነፃነት ጦር ወይም ሸኔ በመባል የሚታወቀው ታጣቂ ተገንጣይ ቡድን ንፁሃን ዜጎችን እንዲሁም የመንግሥት ባለሥልጣናት ላይ ግድያ ፈፅመዋል።" ይላል።

መንግሥት ጥቃት ያደረሰፁ የፀጥታ አካላትን ተጠያቂ ለማድረግ ርምጃ ቢወስድም፣ የመብት ጥሰጥ የፈፀሙና በሙስና የተጠረጠሩ ባለሥልጣናትን ለሕግ ባለማቅረቡ 'ተጠያቂነት እንዳይኖር አድርጓል' ሲል ሪፖርቱ ገልጿል።

በተለያዩ ግጭቶችም ላይ፣ ከሕግ ውጭ በሰላማዊ ሰዎች ላይ ጉዳትና ከባድ በደሎችን ማድረስ፣ አካላዊ ጥቃትን መፈጸም፣ ሰዎችን ማገትና ደብዛቸው እንዲጠፋ መደረጉን ሪፖርቱ ያመለከተ ሲሆን በሰሜን ኢትዮጵያው ግጭት በተለይ በሚሊሻ ቡድኖች፣ የህጻናት ወታደሮችን እንዲሰለፉ መደረጋቸውንም ዘገባው ጠቅሷል፡፡

ሪፖርቱ ህወሓት በጉልበት ህፃናት ለጦርነት እንዲመዘገቡ ማድረጉን የትግራይ ታዳጊ ህፃናት ለቢቢሲ መናገራቸውን ጠቅሶ የኢትዮጵያ መንግሥትም ህፃናትን ለውጊያ እየተጠቀመ መሆኑን ገልፆ ክስ ማሰማቱን አስፍሯል። ሆኖም የህወሃት ቃል አቀባይ ግን ክሱን አለመቀበላቸውን ሪፖርቱ አስታውሷል።

ባለፈው አንድ ዓመት ውስጥ ሐሳብን በነጻነት በመግልጽና በሚዲያዎች ላይ ከባድ ክልከላዎች መካሄዳቸውን፣ ጋዜጠኞች ላይ ዛቻ እንዲሁም ጥቃት እና ያለ ጥፋት እስር መፈፀማቸውን ሪፖርቱ ጨምሮ ያመለከተው ሲሆን የበይነ መረብ ወይም ኢንተርኔት ነጻነትን መከልከል እና ሰዎች በሰላማዊ መንገድና በነጻነት የመሰብሰብ መብት ላይ ጣልቃ መግባት መኖሩም ተብራርቷል፡፡

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ከአካተታቸው ዝርዝሮች መካከልም የጾታ ነክ ጥቃቶችና የሕገ ወጥ የሰዎች ዝውውርን ጨምሮ በተመሳሳይ ፆታ መካከል የሚደረግን ሥምምነት የሚወነጅል ሕግ መኖሩንና በጥቅም ላይ መዋሉን፣ እንዲሁም አነሰተኛ ቁጥር ባላቸው ወይም የተወሰኑ የኅብረተሰብ ክፍሎችንና ቡድኖችን ማጥቃትና ማስፈራራት እንደሚፈፀም ተካተዋል፡፡

የበርካታ ሀገራትን የሰብዓዊ መብት አያያዝ የሚዘረዝረው የዘንድሮ የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሪፖርት ከኢትዮጵያ በተጨማሪ የኤርትራንም የሰብዓዊ መብት አያያዝ ዝርዝር በሪፖርቱ አካቷል።

ኤርትራንም አስመልክቶ ባወጣው ሪፖርት መግቢያ ላይም በኤርትራ እንደ አውሮፓውያን የቀን አቆጣጠር በ1977ዓ ዓ.ም የወጣው ሕገ መንግስት ሥራ ላይ አለመዋሉን ጠቅሶ አገሪቱ በፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ አምባገነናዊ አገዛዝ ስር የምትገኝ መሆኑን አመልክቷል፡፡

እኤአ ከ1993 ዓ.ም ከተደረገው የኤርትራ ነጻነት በኋላ በኤርትራ ምርጫ አለመካሄዱን የሚጠቅሰው ሪፖርት የታጠቁ ኃይሎች ሰላማዊ ሰዎችን በቁጥጥር ስር የማዋል ሥልጣን እንዳላቸውም አመልክቷል፡፡

ሪፖርቱ አክሎ ኤርትራ በሰሜን ኢትዮጵያ እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር ኅዳር 2020 በተቀሰቀሰውና አሁን ድረስ በቀጠለው ጦርነት ጣልቃ በመግባት በኢትዮጵያ ላይ እየተፈጸመ ላለው የሰብአዊ ጥቃት ከፍተኛ አሉታዊ ድርሻ እየተጫወተች መሆኑን አስታውቋል፡፡

"የኤርትራ መከላከያ ሠራዊት በኢትዮጵያ ውስጥ ሰላማዊ ሰዎች ግድያን ጨምሮ በአስገድዶ መድፈር፣ ማሰቃየትና በበርካታ የሰብአዊ መብት ጥሰቶች ተጠያቂ ነው፡፡"

ኤርትራው ውስጥ የሚፈጸሙ በርካታ የሰብአዊ መብቶች ጥሰቶችን ለማስቆም ባለሥልጣናትን ተጠያቂ ለማድረግም ሆነ ምርመራዎችን ለማካሄድ የኤርትራ መንግሥት ምንም ዓይነር እምርጃዎችን የማይወሰድ መሆኑን ሪፖርቱ ጨምሮ አስታውቋል፡፡

አድማጮቻችን በሪፖርቱ ላይ የተጠቀሱትን የኢትዮጵያና የኤርትራ መንግሥትን ጨምሮ የሰብዓዊ መብት ጥሰት ተጠያቂ ናቸው የተባሉትን ድርጅቶችና ቡድኖች ምላሽ በማካተት ሰፊ ዘገባ የምናቀርብ መሆኑን እንገልጻለን፡፡