ተፈናቃዮች ለወራት ርዳታ እንዳላገኙ ቢገልጹም መንግሥት “ቅሬታው ተጋኗል” አለ

የኢትዮጵያ ካርታ

ከኦሮሚያ ክልል የተለያዩ አካባቢዎች ተፈናቅለው በደቡብ ወሎ ዞን ተሁለደሬ እና ከላላ ወረዳዎች በመጠለያ ካምፖች ውስጥ እና ከግለሰቦች ጋራ ተጠግተው የሚኖሩ የኅብረተሰብ ክፍሎች፣ ምንም ዓይነት ርዳታ ሳያገኙ ዐሥር ወራት እንዳለፋቸው ተናገሩ፡፡

ተፈናቃዮቹ ሕይወታቸውን ለማቆየት ልመናን አማራጭ ማድረጋቸውን ገልጸው፣ በምግብ እጥረት ምክንያት በርካቶች ለጤና ችግር መዳረጋቸውን አመልክተዋል፡፡

Your browser doesn’t support HTML5

ተፈናቃዮች ለወራት ርዳታ እንዳላገኙ ቢገልጹም መንግሥት “ቅሬታው ተጋኗል” አለ

የተፈናቃዮቹ ቅሬታ የተጋነነ እንደኾነ የጠቀሰው የደቡብ ወሎ ዞን አደጋ መከላከል እና ምግብ ዋስትና መምሪያ በበኩሉ፣ “ርዳታው ከወር በላይ አልተቋረጠም፤ አሁንም እየተከፋፈለ ነው፤” ሲል ምላሽ ሰጥቷል፡፡

በሌላ በኩል፣ በከላላ ወረዳ የሚገኙ ተፈናቃዮች ሕክምና ለማግኘት የጤና መድኅን ክፍያ እንዲከፍሉ መገደዳቸውን ገልጸዋል፡፡ “አሁን ባለንበት ኹኔታ፣ እንኳን ከፍለን ለመታከም ለዕለት ጉርሳችን እንኳን አናገኝም፤” ሲሉ ቅሬታቸውን አሰምተዋል፡፡

የሕክምና አገልግሎቱ በነጻ እንደሚሰጥ የጠቆሙት የከላላ ወረዳ ጤና ጽ/ቤት ኃላፊ ሐሰን ይማም ደግሞ፣ ክፍያ የሚጠየቅ ተፈናቃይ ቅሬታውን በአካል ለጽ/ቤቱ ኃላፊ ማቅረብ እንደሚችል አስታውቀዋል፡፡

ዝርዝሩን ከተያያዘው ፋይል ይከታተሉ።