ደቡብ ሱዳን የነዳጅ ምርቷን እንደገና ልትጀምር ነው

ጁባ፣ ደቡብ ሱዳን

ደቡብ ሱዳን በዚህ ዓመት መጀመሪያ ላይ በጎረቤት ሱዳን ጦርነት ቁልፉ የነዳጅ ማስተላለፊያ መስመር በመጎዳቱ፣ ተቋርጦ የነበረውን ድፍድፍ ነዳጅ ወደ ውጭ የመላክ ሐሳቧን እንደገና ለመቀጠል ማቀዷ ተገለጸ፡፡

የባሕር በር የሌላት ደቡብ ሱዳን ወሳኝ የሆነውን የነዳጅ ምርቷን በፖርት ሱዳን ወደብ በኩል የመሸጋገሪያውን ወጪ ለሱዳን እየከፈለች ስትልክ ቆይታለች፡፡

የነዳጅ ማስተላለፊያው መስመር በሱዳን ሠራዊትና በፈጥኖ ደራሹ ኃይሎች ጦርነት ሳቢያ በመጎዳቱ ከዓለም አዲሷ ነጻ ሀገር የሆነችውን የደሃይቱን ደቡብ ሱዳንን ኢኮኖሚ በእጅጉ ጎድቶታል፡፡

የነዳጅ ዘይት ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር ኮን ጆን አኮት እ ኤ አ ታኅሣሥ 19 በሀገሪቱ ነዳጅ ለሚያወጣ አንድ ድርጅት በጻፉት ደብዳቤ "የነዳጅ ሚኒስቴር እ ኤ አ ታህሣስ 30 ቀን በምርት ጣቢያ ሦስት እና ሰባት የማምረት ሥራው በይፋ የሚጀምርበት የመክፈቻ ቀን ነው" ማለታቸውን ደብዳቤውን የተመለከተው ኤኤፍፒ ዘግቧል ።

ይሁን እንጂ የነዳጅ ምርቱ ሥራ እንደገና ስለመጀመሩ ከገለልተኛ ወገን ማረጋገጥ አለመቻሉን ኤኤፍፒ ጠቅሷል፡፡

ወደ 12 ሚሊዮን የሚጠጋ ሕዝብ የሚኖርባት ደቡብ ሱዳን እኤአ በ2011 ነፃነቷን ስታገኝ ሦስት አራተኛውን የነዳጅ ክምችት ከሱዳን አብራ ተረክባለች።

የነዳጅ ማስተላለፊያው መስመር ከመበላሸቱ በፊት በቀን ከ150 ሺሕ በርሜል በላይ ድፍድፍ የነዳጅ ዘይት ታመርት እንደነበር በየዓመቱ የዓለምን የኃይል ምንጭ አሃዝ የሚከታተለው የብሪታኒያው የነዳጅ ድርጅት (BP Statistical Review of World Energy) አስታውቋል፡፡

ደቡብ ሱዳን በነዳጅ ሀብት የበለፀገች የዓለማችን አዲሷ ሀገር ብትሆንም ብሔር ተኮር ጥቃትን፣ ሥር የሰደደ አለመረጋጋትን፣ ድህነትን እና የተፈጥሮ አደጋዎችን ታግላ በእግሯ ለመቆም አሁንም እየተፍጨረጨረች ነው፡፡