የደቡብ ኮሪያው ፕሬዝዳንት የአስቸኳይ ጊዜ አስተዳደር አወጁ

  • ቪኦኤ ዜና

የደቡብ ኮሪያው ፕሬዚዳንት ዩን ሰክ ዮል

ተቃዋሚዎች ፓርላማውን በመቆጣጠር ለሰሜን ኮሪያ ያደላ፣ ፀረ-መንግሥት እንቅስቃሴ በማራመድ አገሪቱን ለማሽመደመድ ጥረት እያደረጉ ነው’ ሲሉ የወነጀሉት የደቡብ ኮሪያው ፕሬዚዳንት ዩን ሰክ ዮል አገሪቱን በወታደራዊ ኅግ ለማስተዳደር የሚያስችል የአስቸኳይ ጊዜ ድንጋጌ አውጀዋል።

‘ሰሜን ኮሪያን የሚደግፉ ኃይሎችን ለማጥፋት እና ህገ መንግሥታዊ ዲሞክራሲያዊ ሥርዓቱን ለማስጠበቅ ነው’ ሲሉ እቅዳቸውን ያስታወቁት፤ በቴሌቭዥን ቀርበው ባሰሙት ንግግር ነው። ርምጃው በሀገሪቱ አስተዳደር እና የዴሞክራሲ ሥርዓት ላይ ምን ዓይነት ተጽዕኖ ሊያሳድር እንደሚችል ግን ለጊዜው ግልጽ አይደለም።

በሕዝብ ዘንድ ያላቸው ድጋፍ ባለፉት ቅርብ ወራት ውስጥ በእጅጉ ማሽቆልቆሉ የተዘገበው ዩን፤ በተቃዋሚ ኃይሎች ቁጥጥር ሥር ባለው ፓርላማ ተጽዕኖ የተነሳ ወደ ሥልጣን ከመጡበት እንደ አውሮፓውያን የዘመን አቆጣጠር ከ2022 አንስቶ አስተዳደራቸው የነደፈውን አጀንዳ ለማሳካት ሳይችሉ ቀርተዋል።

ወግ አጥባቂው የዩን ሕዝባዊ ኅይል ‘ፒፕል ፓወር’ ፓርቲ በሚቀጥለው ዓመት የበጀት ረቂቅ ዙሪያ ከተቃዋሚው ‘ሊበራል ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ’ ጋር አጣብቂኝ ውስጥ እንደ ገባ ነው። በሌላ በኩል ዩን፤ በባለቤታቸው እና በከፍተኛ ባለስልጣናት ‘ተፈጽመዋል’ በሚል የተነሱ የወንጀል ቅሌቶች በገለልተኛ አካል እንዲጣሩ የቀረበውን ጥሪ ውድቅ ማድረጋቸው ከፖለቲካ ተቀናቃኞቻቸው ዘንድ ፈጣን እና ብርቱ ትችት ቀስቅሷል።

ዩን ይፋ ያደረጉትን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ተከትሎም ዴሞክራት ፓርቲው በምክር ቤቱ የሚገኙ የሕግ አውጭ አባላቱን ለአስቸኳይ ጉባኤ ጠርቷል።