በደቡብ አፍሪካ የ21 ማዕድን አውጪዎች አስከሬን ተገኘ

  • ቪኦኤ ዜና
የደቡብ አፍሪካ ካርታ

የደቡብ አፍሪካ ካርታ

በደቡብ አፍሪካ ሕገ-ወጥ ማዕድን አውጪዎች ሳይሆኑ አይቀሩም የተባሉ የ21 ሰዎች አስከሬን ከጆሃንስበርግ በስተምዕራብ ባለችው ኩገርስድራፕ በተሰኘች ከተማ በአንድ ማዕድን ማውጫ ሥፍራ አቅራቢያ መገኘቱን የሃገሪቱ ፖሊስ አስታውቋል።

ፖሊስ 19 አስከሬኖችን ትናንት፤ ረቡዕ፣ ሁለት ተጨማሪ አስከሬኖችን ደግሞ ዛሬ ጠዋት ማገኘቱን ገልጿል። ሁለቱ ተጨማሪ አስከሬኖች የተገኙት ለማዕድን ማውጫ በተቆፈረው ጉድጓድ ውስጥ መሆኑን ፖሊስ አስታውቋል።

አሳዛኙ ክስተት ከሕገ-ወጥ ማዕድን ማውጣት ጋር ተያይዞ ሲታዩ ከነበሩ አሰቃቂ ሁኔታዎች አንዱ መሆኑ ሲገለጽ፤ በዚሁ አካባቢ ባለፈው ሐምሌ ለሙዚቃ ፊልም ሥራ የተሰባሰቡ ስምንት ሴቶች ዝርፊያና አስገድዶ መደፈር ተፈጽሞባቸዋል።

ድርጊቱ በአካባባው ማኅበረሰብ ዘንድ ሁከት የተቀላቀለበት ተቃውሞ በሕገ-ወጥ ማዕድን አውጪዎች ላይ እንዲደረግ ምክንያት ሆኖ እንደነበርም ይታወሳል።

ባለፈው ሳምንት 14 ወንዶች በዝርፊያና በአስገድዶ መድፈር ከተከሰሱ በኋላ፣ ፖሊስ የዘረመል ማስረጃ ማቅረብ ባለመቻሉ ክሱ ውድቅ ተደርጓል። ነገር ግን ሃገሪቱ ውስጥ በሕገ ወጥ መንገድ ገብተዋል በሚል ክስ ተመስርቶባቸዋል።

ሕገ-ወጥ ማዕድን አውጪዎች በፖሊስ ዘንድ አደገኛ ተደርገው የሚታዩ ሲሆን፤በአብዛኛው የታጠቁ መሆናቸው ሲገለጽ፣ በማዕድን ሥፍራ በይገባኛል ምክንያት ከተፎካካሪ ቡድኖች ጋር እርስ በእርሳቸው የሚያደርጉት ውጊያም ከበድ ያለ ነው ተብሏል።

እንደ አሶስዬትድ ፕረስ ዘገባ፣ የሕገ-ወጥ ማዕድን ማውጣት ሥራው በአብዛኛው ከሌሶቶ፣ ዚምባብዌና ሞዛምቢክ ወደ ሃገሪቱ በሕገ-ወጥ መንገድ በሚገቡ ሰዎች የሚካሄድ ነው።