መኢአድ ከደቡብ ሰለሚፈናቀሉ ገበሬዎች መግለጫ ሰጠ

  • እስክንድር ፍሬው
“የኢትዮጵያ መንግሥት ተፈናቃዮቹን ከመርዳት ይልቅ እውነታውን በመካድ ፕሮፓጋንዳ ተጠምዷል” - መኢአድ

የመላ ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት መኢአድ የሰጠው መግለጫ የደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል ባለሥልጣናት በተፈናቀሉት ዜጎች ጉዳይ የያዙትን አቋም መነሻ ያደረገ ይመስላል። የክልሉ ፕሬዚዳንት አቶ ሺፈራው ሽጉጤ ሰሞኑን ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ የተፈናቀለ ሰው እንደሌለ ነው የገለፁት።

“ሃያ ሁለት ሺህ ሰዎች ቤንቺ ማጂ ዞን ጉራ ፈርዳ ወረዳ እንደሠፈሩ ነው፤ አልተፈናቀሉም፤ ውሸት ነው” ብለዋል። “የመጡበት ሁኔታ ትክክል ስላልነበረ አካባቢውን ለቅቀው መውጣት የነበረባቸው” ያሏቸው “አንድ ሺህ አንድ መቶ ሃያ ሰዎች ንብረት በማፍራታቸው ከጉራ ፈርዳ እንዳይፈናቀሉ ተደርጓል” ብለዋል።

“በተለያዩ የክልል አካባቢዎች የሠፈሩ ነባሮች ግን ከህዝቡ ጋር ተዋድደውና ተከባብረው ኑሯቸውን ቀጥለዋል፤ የአማራ ብሔር ተወላጆች ከደቡብ እንዲፈናቀሉ ተደርጓል የሚለው ዜና ውሽት ነው” ብለዋል።

በመኢአድ ህዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ጌታቸው አበበ የተነበበው የድርጅቱ መግለጫ ግን የፕሬዚደንቱን አስተያየት አውግዟል።

የክልሉ ፕሬዚዳንት በአገሪቱ መገናኛ ብዙኃን የተናገሩትን “ርካሽ ፕሮፓጋንዳ አሣዛኝና አሣፋሪ ሆኖ አግኝተነዋል” ብለዋል።

“ፕሬዚዳንቱ ፀሐይ የሞቀውን እውነት ለመሸፈን ሲሉ ከክልሉ የተፈናቀለ የለም ማለታቸው ኢሰብአዊ ኢዴሞክራሲያዊና የዜጎችን ክብር የነካና ያዋረደ ነው” ብለዋል።

“መንግሥት በሕዝብ ላይ ለደረሰ ስቃይ ጆሮና ዐይን ሰጥቶ መፍትሔ ከመፈለግ ይልቅ በተራ ፕሮፓጋንዳ መጠመዱን ያሣያል” ብለዋል።

ከጉራ ፈርዳ የሚፈናቀሉ ብሔረ አማራ ገበሬዎች ቁጥር ከነቤተሰባቸው ወደ ሰባ ስምንት ሺህ እንደሚደርስ መኢአድ ጠቁሟል።

እስክንድር ፍሬው ከአዲስ አበባ መግለጫዉን ተከታትሏል፤ አዲሱ አበበም ከዋሽንግተን ቢሯችን ወደ ተፈናቃዮች ስልክ ደውሎ የሰሞኑን ሁኔታ ዘግቧል፡፡

ዝርዝሩን ከዘገባው ያድምጡ።