ተምች በደራሼ ልዩ ወረዳ የደረሱ ሰብሎች ላይ ከፍተኛ ጉዳት ማድረሱ ተገለጸ

Your browser doesn’t support HTML5

ተምች በደራሼ ልዩ ወረዳ የደረሱ ሰብሎች ላይ ከፍተኛ ጉዳት ማድረሱ ተገለጸ

በደቡብ ክልል ደራሼ ልዩ ወረዳ፣ በኮንሶ ዞንና በአካባቢው የተከሠተው አፍሪካን ቦልዎርም የተባለ የተምች ፀረ ቡቃያ ተባይ፣ በደረሰ ማሽላ እና በሌሎች የአዝዕርት ሰብሎች ላይ ከፍተኛ ጉዳት ማስከተሉን፣ አርሶ አደሮች ለአሜሪካ ድምፅ በስልክ ገለጹ።

ተምቹን ለመቆጣጠር፥ በባህላዊ መንገድ የመሰብሰብ እና የመጨፍለቅ ሥራ በመሥራት ላይ እንደኾኑ የገለጹት አርሶ አደሮቹ፣ ከመንግሥት ግን፣ በቂ ክትትል እና ድጋፍ አልተደረገልንም፤ ሲሉ፣ ቅሬታቸውን አሰምተዋል።

በደቡብ ብሔር ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች ክልል ግብርና ቢሮ የአርባ ምንጭ ዕፀዋት ጥበቃ ክሊኒክ፣ በደራሼ እና ኮንሶ፣ እንዲሁም በቆላማ አከባቢዎች፣ አፍሪካ ቦል ዎርም የተሰኘ ተምች መከሠቱን አረጋግጧል።

ተምቹ፣ በደራሼ ልዩ ወረዳ ብቻ፣ በ32 ሺሕ ሄክታር የማሽላ ማሳ ላይ እንደተከሠተ፣ የክሊኒኩ ሓላፊ አቶ ሙሉዓለም መርሻ ጠቅሰው፣ የመከላከል ዘመቻ እየተካሔደ መኾኑን አስታውቀዋል።

በሐዋሳ ዩኒቨርሲቲ የግብርና ኮሌጅ መምህር ዶክተር ፍርዱ አዘረፈኸኝ፣ በአስቸኳይ የመከላከል ሥራ ካልተሠራ፣ ከፍተኛ ውድመት እንደሚያደርስ ገልጸው፣ ፀረ ተባይ ኬሚካል በመርጨት ማጥፋት እንደሚገባ አሳስበዋል።

ዝርዝሩን ከተያያዘው ፋይል ይከታተሉ።