ሶማሊያ 49 የአል-ሻባብ ተዋጊዎችን ገድያለሁ አለች

  • ቪኦኤ ዜና
የሶማሊያ መንግሥት ወታደሮች

የሶማሊያ መንግሥት ወታደሮች

በዓለም አቀፍ ኃይሎች የሚደገፈው ጦሯ በታችኛው ሸበሌ ክልል ባደርገው ዘመቻ 49 የአል-ሻባብ ተዋጊዎችን መግደሉን ሶማሊያ ዛሬ አስታውቃለች።

የቪኦኤው ሞሃመድ ዳህይሴን ከሞቃዲሹ እንደዘገበውና የሶማሊያ ማስታወቂያ ሚኒስቴር ትናንት ማምሻውን ባወጣው መግለጫ፣ ወታደራዊ ዘመቻው የተካሄደው ቡሎ ማዲኖ በተሰኘው በታችኛው ሸበሌ ክልል በሚገኝ መንደር ነው።

ቪኦኤ መንግሥት ገደልኩ የሚለውን የሟቾች ቁጥር ማረጋገጥ ባይችልም፣ በአካባቢው ያሉ ነዋሪዎች ግን ፍንዳታ መስማታቸውን ተናግረዋል።

“በኻዋሪጅ አል-ሻባብ ላይ አነጣጥሮ የተወሰደው ጥቃት ወታደራዊ መጓጓዛዎችንንና ትጥቆችን አውድሟል” ሲል የማስታወቂያ ሚኒስቴሩ መግለጫ አውስቷል።

መንግስት እንደሚለው አክራሪ ተዋጊዎቹ የተመቱት “የሶማሊያን ህዝብ ለማጥቃት በተዘጋጁበት ወቅት ነው።” መግለጫው በተጨማሪም የአየር ድብደባ መካሄዱን ጠቅሷል። የትኛው አገር በአየር ጥቃቱ እንደተሳተፈ ያለው ነገር የለም።

ጥቃቱ የመጣው ፕሬዚዳንት ሃሳን ሼክ ሞሃመድ፣ ሂራን እና ጋልጋዱድ የተባሉትን የግንባር ከተሞች ከጉበኙ ከጥቂት ቀናት በኋላ ነው።

አል-ሻባብ ሼክ ሞሃመድ ፕሬዝደንት ሆነው ከተመረጡ በኋላ ጥቃቱን አጠናክሯል። ፕሬዝደንቱም በቡድኑ ላይ አጠቃላይ ጦርነት አውጀዋል።

ከቡድኑ ጥቃት በቅርቡ ከሚጠቀሱት፣ ወደ ኢትዮጵያ በመግባት የፈጸመውና በመቶ የሚቆጠሩ ተዋጊዎቹ አልቀውበታል የተባለውና፣ በሁለት መኪና በተጠመዱ ቦንቦች በሞቃዲሹ 120 ሰዎችን የገደለበት ይገኛሉ።