የኬንያ ወታደራዊ እንቅስቃሴ

በቅርቡ ኬንያ ውስጥ የተጠለፉት ፈረንሣዊት ማሪ ዴዲዮ

ኬንያ ወደሶማሊያ አጎራባች አካባቢዎች የጦር ኃይሏን ለማስገባት የወሰደችው ውሣኔ ሃገሪቱ እስከአሁን ስትከተለው በቆየችው የውጭ ፖሊሲዋ ላይ መሠረታዊ ለውጥ የሚያመጣ መሆኑ ተወርቷል፡፡

የኬንያ ወታደራዊ ዘመቻ ሙሉ ስፋቱ ምን ያህል እንደሚሆን ገና ግልፅ ባይሆንም እንቅስቃሴው በራሱ ግን በሁለቱ ሃገሮች መካከል ያለውን የግንኙነት ዓይነት እንደሚለውጠው እየተነገረ ነው፡፡

ኬንያ ከሥርዓት ከጠፋባት፤ ትምርስ፣ ሞትና ስደት ከነገሡባት ጎረቤቷ ጋር ለዓመታት ተፋጥጣ ኖራለች፡፡ ሶማሊያን ከሃያ ዓመታት በላይ ቀስፎ በያዛት የርስበርስ ጦርነትና ፍጅት ምክንያት አገሩን እየጣለ የሚነጉደው ሰው መድረሻና መጠለያ ከሆኑ የአካባቢው ምድሮች አንዷ ኬንያ ሆና ቆይታለች፡፡ ይህ ሁኔታ ታዲያ የሃብቱን ያለልክ መወጠርና መመናመን፣ የተፈጥሮውን አካባቢ ከዕለት ወደዕለት እያዘቀጠ መምጣት አስከትሏም፡፡ አንዳንዴም ትዕግሥትን የሚፈታተኑ አድራጎቶች በዚያ እንደሚፈፀሙ ይሰማል፡፡

ካለፉት የመከራ ዓመታት የበለጠውን ጊዜ ታዲያ ኬንያ እራሷን ከነዚያ ግጭቶችና ብጥብጥ አርቃ፣ እጆቿን ሰብስባ መቀመጥን መርጣ ቆይታለች፡፡ በርግጥ አሁን ሞቃዲሾ ያለው የሽግግሩ ፌደራል መንግሥት ሲመሠረት ቁልፍ ሚና ተጫውታለች፡፡ እንዲያውም የዛሬ ስድስት ዓመት አካባቢ የነበሩት የመንግሥቱ አንዳንድ ተቋማት ዋና ፅ/ቤታቸውን ናይሮቢ ላይ አድርገው ከዚያውም የሶማሊያ ውስጥ ሥራቸውን ሲመሩ መቆየታቸው የቅርብ ጊዜ ትውስታ ነው፡፡

በቅርብ ወራት ውስጥ ኬንያ ውስጥ የሚታየውና የሚፈፀመው በሶማሊያ ታጣቂ አማፂያን ነው የሚባለው የጠለፋዎች መበራከት ግን በኬንያዊያኑ ዘንድ ውጥረት፣ ሥጋትና ቁጣንም የፈጠረ ይመስላል፡፡ የኬንያ ምጣኔ ኃብት የጀርባ አጥንት ናቸው ከሚባሉት ዘርፎች አንዱ የሆነውን የቱሪዝም ኢንዱስትሪዋንም በእጅጉ እያስፈራራና አደጋ ላይ እየጣለ የመጣ ክስተት ሆኗል፡፡

ሰሞኑን በዳዳብ የስደተኞች መጠለያ ሠፈሮች አካባቢ የሁለት ሃኪሞች መጠለፍ ጉዳይ ባለፈው ሣምንት የመጨረሻ ቀናት የኬንያ ጦር ኃይሎች ለእርምጃ እንዲነሣሱ ቆስቁሷቸዋል ተብሏል፡፡

ይህ የጦሩ እርምጃ እንዳላስደነገጣቸው የሃገሪቱ የቀድሞ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አማካሪ ኤጋራ ካባጂ ሲናገሩ "ኬንያ መልካም ጉርብትናን የምትከተል ሃገር መሆኗ ይታወቃል፡፡ ይህ ግን ያፈጠጠ ጠብ አጫሪነት ነው፡፡ ያፈጠጠ ጠብ አጫሪነት ደግሞ አፀፋ ይገባዋል፡፡ አንድ ለእኔ ግልፅ የሆነልኝ ነገር ይህ የኬንያ መንግሥት ሊወስድ የሚችለው እጅግ ትክክለኛ የሆነ አቋም ነው፡፡ ምክንያቱም ወንበዴዎች ግዛትህ ውስጥ ገብተው ኢኮኖሚህን ሲያወድሙ እጆችህን አጣጥፈህና ተደላድለህ ተቀምጠህ መልካም ጉርብትናን አራምዳለሁ ማለት አትችልም፡፡ እንደዚያ አይደረግም" ብለዋል፡፡

ወታደራዊ እንቅስቃሴዎቹን በተመለከተ ከናይሮቢም፣ ከሞቃዲሾም እየወጡ ያሉት መረጃዎች የሚናገሩት አንዳንዴም የተጋጨ፣ በሌላ በኩል ደግሞ የኬንያን ጦር ኃይሎች እንቅስቃሴ አስመልክቶ ከሚሰማው የተለየ ነው፡፡

የኬንያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ለሃገራቸውና ለውጭም መገናኛ ብዙኃን የጦር ሠራዊታቸው የሶማሊያን ድንበር ዘልቆ መግባቱን ተናግረዋል፡፡ ሌሎች ባለሥልጣናት ደግሞ "የለም፤ ሠራዊታችን ከወሰናችን አላለፈም" ይላሉ፡፡

የሶማሊያው የሽግግር መንግሥታ ቃል አቀባይ ኦማር ኦስማንም የገለፁት የኬንያ ጦር የሃገራቸውን ድንበር ጥሶ እንዳልገባ ነው፡፡

"ኬንያዊያኑ ወደእኛ ግዛት እንዳልገቡ አረጋግጣለሁ፡፡ የገቡት በኬንያ ሥልጠና ሲሰጣቸው የነበሩ የራሣችን ወታደሮች ናቸው፡፡ ከአልሻባብ ጋር ለመግጠም ከኬንያ የገቡ ሶማሊያዊያን ናቸው፡፡ ኬንያና ሶማሊያ የጋራ ባላንጣ አላቸው፡፡ እርሱም አልሻባብ ነው፡፡ የሎጂስቲክስና ሌሎችም ድጋፎችን ከኬንያ ባለሥልጣናት በማግኘታችን ደግሞ እናመሠግናለን" ብለዋል ቃልአቀባዩ ኦማር ኦስማን፡፡

አንድ በወሰን አካባቢ የነበሩ እማኝ የኬንያ ተዋጊ ጄቶች በቅርብ ቀናት ድንበሩን እያቋረጡ ወደ ሶማሊያ ሲገቡና ሲወጡ ማየታቸውን ለአሜሪካ ድምፅ ተናግረዋል፡፡

ለወትሮው ጥያቸዋለሁ ለሚላቸው ጥቃቶች ኃላፊነቱን ፈጥኖ የሚወስደው አልሻባብ በጠለፋዎቹ ውስጥ እጁ እንደሌለ ገልፆ አሁን ኬንያ እያካሄደች ነው ለሚባለው ወታደራዊ እንቅስቃሴ ግን አፀፋ እንደሚሰጥ ዝቷል፡፡ ከአንድ ዓመት በፊት ካምፓላ ውስጥ የተፈፀመውንና ለሰባ አራት ሕይወት መጥፋት ምክንያት የሆነውን ጥቃት ያደረሰው እርሱ እንደነበረ አልሻባብ በወቅቱ ተናግሯል፡፡

ናይሮቢ ለሚገኝ ሣውዝ ሊንክ ከንሰልታንትስ ለሚባል ድርጅት የሚሠሩት ሶማሊያዊው የፖለቲካ ተንታኝ አብዲ ሣማድ እንዲያ ዓይነት ጥቃቶችን ኬንያ ውስጥ ጠብቁ የሚል መልዕክት ያለው አስተያየት ሰጥተዋል፡፡

"ኬንያ አልሻባብን ከማዕከላዊና ከደቡብ ሶማሊያ ለመንቀል የምትንቀሣቀስ ከሆነ ያለጥርጥር ለበቀል ይሄዳሉ፡፡ በርግጥ አልሻባቦች ባለሙያ ወታደሮች አይደሉም፡፡ የሚያደርጉት ምንድነው? በአንድ ወቅት ካምፓላ ውስጥ የፈፀሙትን እዚህም ይደግሙታል፡፡ ናይሮቢ ውስጥ ትርምስ ሊፈጥሩ ይችላሉ፡፡ ይህንን ያደርጋሉ፡፡ በመሆኑም ሃገሪቱ የጦርነት ሁኔታ ውስጥ ትገባለች ማለት ነው፡፡"

ልምዶችን የተንተራሱ ዘገባዎች እንደሚጠቁሙት ሶማሊያ ውስጥ ያለፉ ወታደራዊ ጣልቃ ገብነቶች የአሁኑን ኬንያዊያኑ ገብተውበታል የተባለውን የጦር እንቅስቃሴ የሚያበረታትቱ አይደሉም፡፡

አልሻባብኢትዮጵያ ጦሯን የዛሬ ሁለት ዓመት አካባቢ እንድታስወጣ እንዳስገደዳት ይነገራል፡፡ እንዲያውም ያ የኢትዮጵያ የሁለት ዓመት ተኩል ወረራ የአልቃይዳ ግብር አበር ለሆነው ለአልሻባብ ከሶማሊያዊያኑ ብዙ ድጋፍ እንዲሸምት ዕድል ሰጥቶታል ነው የሚባለው፡፡

የአሜሪካ ጦር በአውሮፓ አቆጣጠር በ1992 ዓ.ም (የዛሬ ሃያ ዓመት አካባቢ መሆኑ ነው) ወደ ሶማሊያ ገብቶ ነበር፡፡ የአሜሪካ የመጀመሪያ እንቅስቃሴዋ ሰብዓዊ ዕርዳታ ነበር፡፡ ሶማሊያዊያኑ ታጣቂዎች የዩናይትድ ስቴትስን ሄሊኮፕተሮች መትተው ከጣሉና 18 አሜሪካዊያን ወታደሮች ከተገደሉ በኋላ ያ ዘመቻ አበቃ፡፡

አሁን የኬንያ መንግሥት የሚለው እያካሄደ ያለው ዘመቻ ዓላማ አልሻባብ ኬንያ ውስጥና በድንበሮቹም አካባቢ ዳግመኛ አለመመላለሱንና አለመንቀሣቀሱን ማረጋገጥ ነው፡፡ ይህ ዘመቻ ለምን ያህል ጊዜና በምን ያህል ስፋት የሚካሄድ መሆኑን የሚናገር መረጃ እስከአሁን ከየትም ወገን አልተሰማም፡፡

ዘገባውን ያዳምጡ፡፡