የኢትዮጵያው የውጪ ጉዳይ ምኒስትር ታዬ አጽቀ ስላሴ “የውጪ ኃይሎች” ለሶማሊያ መሣሪያ ማቀበላቸው “የተዳከመውን የፀጥታ ሁኔታ የሚያባብስ እና መሣሪያውም በሶማሊያ በሚገኙ አሸባሪዎች እጅ ሊወድቅ ይችላል” ብለው መናገራቸውን ተከትሎ፣ የሶማሊያው የውጪ ጉዳይ ሚኒስትር ነቀፌታ አሰምተዋል።
የሶማሊያው የውጪ ጉዳይ ምኒስትር አህምድ ሞአሊም ፊቂ ለሮይተርስ የዜና ወኪል እንዳሉት “ስም አጥፊ” ብለው የጠሩት የኢትዮጵያ መግለጫ፣ “በሕገ ወጥ መንገድ በሶማሊያ ድንበር እየገባ በሲቪሎች እና አሸባሪዎች እጅ የሚወድቀውን መሣሪያ ሁኔታ ለመደበቅ የሚደረግ ሙከራ ነው” ብለዋል። ፋቂ ለክሳቸው ምንም ዓይነት ማስረጃ እንዳላቀረቡ የሮይተርስ ዘገባ አመልክቷል።
SEE ALSO: ኢትዮጵያ ግብጽ በሳምንቱ መጨረሻ ወደሶማሊያ በድጋሚ የጦር መሣሪያዎች መላኳን በሚመለከት ያላትን ሥጋት ገለጸችፋቂ አክለውም፣ “ኢትዮጵያ የሶማሊያን ሉዓላዊነት በመዳፈርዋ ላይ ያለውን ትኩረት ለማስቀየስ እየሞከረች ነው” ብለዋል።
ኢትዮጵያ ወደ ፑንትላንድ መሣሪያ ታስገባለች ስትል ሶማሊያ ባለፈው ሳምንት ኢትዮጵያ ላይ ክስ አሰምታ ነበር። ኢትዮጵያ በክሱ ላይ እስከ አሁን መልስ አልሰጠችም።
ኢትዮጵያ ከሶማሊላንድ ጋራ የባሕር በር አጠቃቀምን በተመለከተ የተፈራረመችው የመግባቢያ ስምምነት ውጥረት ፈጥሮ ባለበት ሁኔታ፣ መሣሪያ ወደ ሶማሊያ መላኳን ግብፅ በዚህ ሳምንት አስታውቃለች፡፡
ግብፅ መሣሪያውን ወደ ሶማሊያ የላከችው፣ “ሶማሊያ ፀጥታና መረጋጋት ለመፍጠር የምታደርገውን ጥረት፣ ከአሸባሪዎች ጋራ የምታደርገውብ ፍልሚያ እና ግዛትና አንድነቷን ለመጠበቅ የምታደርገውን ጥረት ለመደገፍ የምታደርገው የዕርዳታ ማእቀፍ አካል” እንደሆነ አስታውቃለች፡፡