በኢትዮጵያ እና በሶማሊያ መካከል ቱርክ ላይ ትላንት የተካሄደው ሁለተኛው ዙር ውይይት ካለስምምነት በመጠናቀቁ፣ ሁለቱ ወገኖች ለሶስተኛ ዙር ውይይት መስከረም 7 ቀን 2017 ዓ/ም ለመገናኘት ቀጠሮ መያዛቸውን ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው ሁለት ምንጮች ለቪኦኤ የአፍሪካ ቀንድ ክፍል አስታውቀዋል።
ከጉዳዩ አሳሳቢነት የተነሳ ማንነታቸው እንዳይገለጽ የፈለጉት ምንጮች እንዳሉት፤ ሶማሊያ፣ ኢትዮጵያ የባሕር በር አጠቃቀምን በተመለከተ ከሶማሊላንድ ጋራ የተፈራረመችውን የመግባቢያ ስምምነት እንድትሰርዝ ስትጠይቅ፤ ኢትዮጵያ በበኩሏ ደግሞ ሶማሊያ ቀድማ የባሕር በር አጠቃቀምን በተመለከተ ስምምነት እንድትፈጸም ጠይቃለች፡፡
SEE ALSO: የኢትዮጵያና የሶማሊያ የውጪ ጉዳይ ሚኒስትሮች ሁለተኛ ዙር ውይይት ሊያደርጉ ነውምንጮቹ እንዳሉት፣ ከመግባቢያ ስምምነቱ ኢትዮጵያ የምትወጣበት የቋንቋ አገላለጽ፣ እንዲሁም የባሕር በር መጠቀም የሚያስችላትን ሁኔታ አስመልክቶ የሚሰፍረው የቋንቋ አገላለጽን በተመለከተ በሁለቱ ወገኖች መካከል ልዩነት በመኖሩ ስምምነት ላይ እንዳይደርሱ እንቅፋት የሆነ ዋና ጉዳይ ነው።
ኢትዮጵያ የባሕር በር መጠቀም ትችል ዘንድ ከሶማሊላንድ ጋራ ባለፈው ታህሳስ የመግባቢያ ስምምነት መፈራረሟ ከሶማሊያ ጋራ ቅራኔ ውስጥ እንዲገቡ አድርጓል። ይህን ተከትሎ ቱርክ ለማሸማገል ጥረት በማድረግ ላይ ነች፡፡
ስምምነቱ ኢትዮጵያ 20 ኪ/ሜ የሚደርስ የባሕር ዳርቻ ከሶማሊላንድ በሊዝ ለመያዝና የባሕር ኃይል መሠረት ለመገንባት የሚያስችላት መሆኑ ተነግሮ ነበር። ኢትዮጵያ በምትኩ ሶማሊላንድን እንደ አንድ ነፃ ሃገር እውቅና ትሰጣለች ተብሉ ቢነገርም የኢትዮጵያ ባለሥልጣናት ይህን በይፋ አላረጋገጡም።
ከሶማሊያ ተገንጥላ ራሷን ከምታስተዳድረው ሶማሊላንድ ጋራ የተፈጸመው ስምምነት ሉአላዊነቷንና የግዛት አንድነቷን የሚጋፋ እንደሆነ በመግልጽ ሶማሊያ ስምምነቱን አውግዛለች፡፡
ሁለቱ ወገኖች ውይይቱን ሲያደርጉ የነበረው በቀጥታ ፊት ለፊት ሳይሆን ‘በስማ በለው’ እንደሆነ ምንጮቹ አስታውቀዋል። የቱርኩ የውጪ ጉዳይ ምኒስትር ሃካን ፊዳን፣ ከሶማሊያው የውጪ ጉዳይ ምኒስትር አህመድ ሞዋሊም ፊቂ እንዲሁም ከኢትዮጵያው የውጪ ጉዳይ ምኒስትር ታዬ አጽቀስላሴ ጋራ ለየብቻ እንደተነጋገሩ ለማወቅ ተችሏል።
ትላንት ከተደረገው የሁለተኛው ዙር ውይይት ቀደም ብሎ፣ የቱርኩ ፕሬዝደንት ረችፕ ታይፕ ኤርዶዋን፣ የኢትዮጵያውን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ እንዲሁም የሶማሊያውን ፕሬዝደንት ሃሳን ሼክ ሞሃሙድ በስልክ በማነጋገር ልዩነቶቻቸውን እንዲፈቱ አበረታተዋል።