ሶማሊያ የኢትዮጵያ ኅይሎች “ሳይነኩና ባልተጠበቀ” ባለችው ሁኔታ በሁለቱ ሀገራት ድንበር መካከል በሶማሊያ በኩል ባለችው ዶሎው ከተማ ላይ በሚገኝ ሠራዊቷ ላይ ጥቃት ፈጽመዋል ስትል ከሳለች፡፡
የሶማሊያ የውጪ ጉዳይ ሚኒስቴር በአወጣው መግለጫ፣ የኢትዮጵያ ኅይሎች ዛሬ ጠዋት አራት ሠዓት ላይ በከተማዋ በሶማሊያ መንግሥት ኅይሎች ሥር በነበሩ ሶስት ይዞታዎች ላይ የኢትዮጵያ ኅይሎች ጥቃት ፈጽመዋል ብሏል።
ድርጊቱ የአንካራውን ስምምነት የጣሰ ነው ስትልም ሶማሊያ አስታውቃለች፡፡
ከኢትዮጵያ ጋራ በምትዋሰነው የሶማሊያዋ ዶሎው ከተማ በጁባላንድ ኅይሎች እና በሶማሊያ የመንግሥት ወታደሮች መካከል ዛሬ ግጭት መከሰቱ ቀደም ብሎ ተነግሮ ነበር።
በከተማይቱ በርካታ የኢትዮጵያ ወታደሮች ይገኛሉ። ከተማዋ በአብዛኛው ሞሃመድ ሁሴን አብዲ ላፌ በተባሉ ኮሚሽነር ሥር የምትደዳር ሲሆን፣ ኮሚሽነሩ ከኢትዮጵያ ኅይሎች ጋራ የቅርብ ግንኙነት እንዳላቸው ታውቋል።
አንድ የከተማዋ ነዋሪ የኢትዮጵያ ኅይሎች ለኮሚሽነሩ ኅይሎች “ወግነዋል” ሲል ተናግሯል። ተፈጥሯል የተባለውን ክስተት በተመለከተ ከኢትዮጵያ ወገን ወዲያውኑ የተሰጠ ምላሽ የለም። ቪኦኤ በዛሬው ዶሎው ተከስቷል ስለተባለው ግጭት የኢትዮጵያ ኅይሎችን ሚና በገለልተኛ ወገን አላረጋገጠም።
ይህ በእንዲህ እንዳለ የሶማሊያ መንግሥት ሁለት ባለሥልጣናትን ዛሬ ሰኞ ወደ ግብፅ እና ኢትዮጵያ መላኩ ታውቋል። የሶማሊያው የውጪ ጉዳይ ምኒስትር አህመድ ሞአሊም ፊቂ ካይሮ ተገኝተው ከሀገሪቱ የውጪ ጉዳይ ምኒስትር ባድር አብደላቲ ጋራ እንደተነጋገሩ ሲታወቅ በሌላ በኩል ደግሞ የውጪ ጉዳይ ምኒስትር ዴታ አሊ ሞሃመድ ኦማር ወደ አዲስ አበባ መጓዛቸው ታውቋል።
የሶማሊያው የውጪ ጉዳይ ሚኒስቴር በአወጣው መግለጫ ብፊቂ እና በአብደላቲ መካከል የተደረገው ውይይት ታሪካዊ ግንኙነታቸውን በማጠናከር፣ እንዲሁም በፀጥታ፣ ፖለቲካ፣ ትምህርት፣ እና የኢኮኖሚ ልማትን በተመለከቱ ጉዳዮች ላይ ያተኮረ እንደነበር አስታውቋል።
ሁለቱ ምኒስትሮች “ውጤታማ ውይይት” አድርገዋል ሲሉ የግብጹ የውጪ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ታሚም ካላፍ አስታውቀዋል።
ሁለቱ ምኒስትሮች “ የሁለትዮሽ ግንኙነታቸውን በሚያጠናክሩበት፣ በፀረ ሽብርተኝነት ላይ በሚደረግ ትብብር፣ እንዲሁም በሶማሊያ የአፍሪካ ኅብረት የማረጋጋትና ድጋፍ ልዑክ ምሥረታ በሚሳለጥበት መንገድ ላይ ተወያይተዋል” ሲሉ ቃል አቀባዩ በX ማኅበራዊ መድረክ ላይ አመልክተዋል።
በሌላ በኩል ደግሞ የውጪ ጉዳይ ምኒስትር ዴታ አሊ ሞሃመድ ኦማር፣ የቱርክ መንግስት የኢትዮጵያን የባሕር በር ጥያቄ አስመልክቶ አንካራ ላይ ስምምነት እንዲፈረም ባስቻለ በጥቂት ግዜያት ውስጥ ወደ አዲስ አበባ መጓዛቸው ታውቋል።
የሶማሊያው የውጪ ጉዳይ ሚኒስቴር ባወጣው መግለጫ “ጉብኝቱ ሶማሊያ ከኢትዮጵያ ጋራ ለሚኖራት የሁለትዮሽ ግንኙነት ያላትን የማያወላውል ቁርጠኝነት የሚያመለከት ነው” ብሏል።
”ጉብኝቱ በጋራ መከባበር፣ በጋራ ፍላጎትና ትብብር ላይ የተመሠረቱ ተሻጋሪ መልካም አጋጣሚዎች ላይ ያተኮረ ነው” ሲልም አክሏል።