የእስላማዊ ቡድን ማንሰራራት ያሰጋት ሶማሊያ ለቀው የሚወጡት ሰላም አስከባሪ ኃይሎች ፍጥነት እንዲቀንሱ ጠየቀች

የሶማሊያ ካርታ

በሀገሯ የጸጥታ ክፍተት ሊፈጠር ይችላል ስትል ያስጠነቀቀችው ሶማሊያ፣ የአፍሪካ ሰላም አሰከባሪ ኃይሎች ከሶማሊያ ለቀው የሚወጡበትን ፍጥነት እንዲቀንሱ ጠይቃለች። ሮይተርስ የተመለከታቸው ሰነዶች እንደሚያሳዩት፣ ከሶማሊያ ጋር ድንበር የሚዋሰኑ አጎራባች ሀገሮች፣ ዳግም እያንሰራራ የሚገኘው የአል-ሻባብ ቡድን ስልጣን ሊቆጣጠር ይችላል የሚል ስጋት ገብቷቸዋል።

በሶማሊያ የሚገኘው የአፍሪካ ህብረት የሽግግር ተልዕኮ (አትሚስ) ሰላም አስከባሪ ኃይል እ.አ.አ በታህሳስ መጨረሻ ሙሉ ለሙሉ ሶማሊያን ለቆ ለመውጣት ዝግጅቱን የጨረሰ ሲሆን፣ በቁጥር አነስተኛ የሆነ ኃይል በቦታው እንደሚተካ ይጠበቃል።

ሆኖም የሶማሊያ መንግስት ለአፍሪካ ህብረት ሰላም እና ጸጥታ ምክርቤት ጊዜያዊ ሊቀመንበር ባለፈው ወር በላከው ደብዳቤ፣ አሁን ካሉት 4ሺህ ወታደሮች ግማሽ የሚሆኑን እስከ ሰኔ ወር መጨረሻ ለማስወጣት የተያዘውን እቅድ ወደ መስከረም እንዲያሻግር ጠይቋል። መንግስት ቀድም ሲል ለህብረቱ አስገብቶት በነበረው እና ሮይተርስ በተመልከተው ሰነድም፣ ሰላም አስከባሪው ኃይል ለቆ የሚወጣበት ጊዜ በሶማሊያ ኃይሎች "ዝግጁነት እና አቅም ላይ እንዲመሠረት" ጠይቆ ነበር።

በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የፀጥታው ምክርቤት ተልዕኮ የተሰጠው ቡድን ባካሄደው የጋር ግምገማም "የአፍሪካ ህብረት ሰላም አስከባሪ ኃይል በችኮላ መውጣታቸው የፀጥታ ክፍተት እንደሚፈጥር" አስጠንቅቋል።

የፓርላማው መከላከያ ኮሚቴ ገለልተኛ አባል የሆኑት ሙርሳል ካሊፍ ባደረጉት ንግግር "የትውልድ ሀገሬ እየሄደችበት ያለው አቅጣጫ በዚህ መጠን አስግቶኝ አያውቅም" ብለዋል።

በሶማሊያ ለሚገኘው የአፍሪካ ህብረት ኃይል ከፍተኛ የገንዘብ ደጋፊ የሆኑት ዩናይትድ ስቴትስ እና የአውሮፓ ህብረት የሰላም አስከባሪውን ኃይል ለመቀነስ የወሰኑት፣ ዘላቂነት ያለው የረጅም ጊዜ የገንዘብ ድጋፍ የማድረጉ ሁኔታ ስጋት ውስጥ ስለከተታቸው መሆኑን አራት የዲፕሎማቲክ ምንጮች እና አንድ የዩጋንዳ ከፍተኛ ባለስልጣን ለሮይተርስ ተናግረዋል።

የሶማሊያ ፕሬዝዳንት እና የጠቅላይ ሚኒስትር ፅህፈት ቤት በጉዳዩ ላይ አስተያየት እንዲሰጡ ለቀረበላቸው ጥያቄ ምላሽ አልሰጡም።