የሶማሊያ ኃይሎች በርካታ የአልሻባብ ታጣቂዎችን መግደላቸው ተገለጸ

  • ቪኦኤ ዜና

ደቡባዊ ሶማሊያ ጁባላንድ ክፍለ ግዛት ውስጥ በተቀሰቀሰ አዲስ ውጊያ በርካታ የአልሻባብ ተዋጊዎች ተገድለዋል ሲሉ የሀገሪቱ ባለሥልጣናት ተናገሩ።

ውጊያው የተቀሰቀሰው የቡድኑ ታጣቂዎች ከኪስማዮ ከተማ በስተሰሜን እና በስተደቡብ በሚገኙ የፌዴራል እና የክፍለ ግዛት ሠራዊቶች ሰፈሮች ላይ ያደረሱትን የተቀናጀ ጥቃት ተከትሎ መሆኑን ባለስልጣናቱ ገልጸዋል።

የጁባላንድ ክልላዊ ኃይሎች አዛዡ ለቪኦኤ በሰጡት ቃል 135 ታጣቂዎች ገድለናል ብለዋል። ጥቃት በተሰነዘረባቸው የጦር ሰፈሮች ወታደሮች ያሉት ፊዴራል መንግሥቱ በበኩሉ ስለተገደሉት ታጣቂዎች ከክልላዊ ኃይል የተለየ አሃዝ የሰጠ ሲሆን 80 ታጣቂዎች ገድለናል ብሏል።

በሁለቱ ወገኖች የቀረቡትን አሃዞችም ይሁን የቪዲዮ ምስሎች ቪኦኤ በሌላ ምንጭ ለማረጋገጥ አልቻለም።