ኢትዮጵያ "ያልተፈቀዱ የጦር መሳሪዎችን እና ጥይቶችን" ወደ ሶማሊያዋ ከፊል ራስ ገዝ አስተዳደር ፑንትላንድ ልካለች’ ሲል የሶማሊያ መንግሥት ዛሬ አርብ ባወጣው መግለጫ ከሷል።
የተባለውን ድርጊት “በጽኑ ታወግዛለች” ያለው የሶማሊያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መግለጫ፤ ኢትዮጵያ በሁለት ወታደራዊ ተሽከርካሪዎች የተጫነውን የጦር መሳሪያ ወደ ፑንትላንድ በሚወስደው የገዛ ግዛቷ በኩል አሳልፋ ታጓጉዛለች” ሲል ከሷል። አያይዞም አንዳችም ዲፕሎማሲያዊ ተሳትፎ ወይም ፈቃድ በሌለበት የተፈጸመው እርምጃ፣ በሶማሊያ ሉዓላዊነት ላይ ከፍተኛ ጥሰት የፈጸመ እና በብሔራዊ ክልሏ ደህንነት ላይም ከፍተኛ ተጽዕኖ የሚያሳድር ነው” ብሎታል። ሆኖም የተባለው የጦር መሳሪያ ጭነት ፑንትላንድ መቼ እንደ ደረሰ መግለጫው አላብራራም።
ድርጊቱ የተፈጸመበትን ጊዜ ያልገለጸው መግለጫ በተጨማሪም ‘ኢትዮጵያ የጦር መሳሪያዎችን ወደ ደቡብ ምዕራብ ሶማሊያ ባይዶዋ በአውሮፕላን ልካለች’ ሲል ከሷል።
የሶማሊያን ውንጀላ አስመልክቶ የአሜሪካ ድምጽ የአፍሪካ ቀንድ አገልግሎት የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚንስቴር ባለሥልጣናት ቢጠይቅም፤ በኢትዮጵያ በኩል እስካሁን ምላሽ አላገኘም።