የኦብነግ መግለጫና የሶማሌ ክልል መንግሥት ምላሽ

Your browser doesn’t support HTML5

የኦብነግ መግለጫና የሶማሌ ክልል መንግሥት ምላሽ

ተቃዋሚው የኦጋዴን ብሔራዊ ነጻ አውጭ ግንባር (ኦብነግ)፣ የሶማሌ ክልል የዜጎች መብት የሚጣስበት እየሆነ ነው ሲል ከሰሰ። ፓርቲው ባለፈው ረቡዕ መስከረም 8 ቀን 2016 ባወጣው መግለጫ፣ ክልሉ ሶማሌዎች ማንነታቸውን እንዲክዱ የሚገደዱበት እየሆነ ነው ብሏል። የክልሉን ስያሜና ሰንደቀላማ የመቀየር እቅድ እንዳለ ከአሉባልታ ከፍ ያለ መረጃ አለን ሲሉም፣ የፓርቲው ሊቀመንበር አቶ አብዲራህማን መሀዲ ለአሜሪካ ድምጽ ተናግረዋል። ባለፉት 6 አመታት በክልሉ የጎሳ ግጭቶች ጨምረዋል ሲሉም ወቀሳ አቅርበዋል።

የክልሉ ርዕሰመስተዳድር አቶ ሙስጠፋ ሙሁመድ በበኩላቸው፣ የክልሉ የሀገር ሽማግሌዎች "እኛ ሶማሌዎች እንጂ ሶማሊያውያን አይደለንም" ማለታቸው ማንነትን እንደመካድ ሊወሰድባቸው አይገባም ብለዋል።

በቀድሞው አስተዳደር ህግን ባልተከተለ መንገድ ተቀይሮ የነበረውን ስያሜና ሰንደቅ አላማ በመተው በህገመንግስቱ የተቀመጠውን ስያሜ መጠቀም የጀመረው የእርሳቸው አስተዳደር መሆኑን የተናገሩት አቶ ሙስጠፋ የኦብነግ ሊቀመንበር የሚመሩት ቡድን ይህንን መግለጫ ያወጣው በክልሉ ችግር ስላለ ሳይሆን "ሰሞኑን በአፍሪካ ቀንድ እየተስተዋለ ያለውን ጂኦፖለቲካዊ ለውጥ ተከትሎ ጥቅም በመፈለግ ነው" ሲሉ ተችተዋል።