የብልፅግና ፓርቲ ከፍተኛ አመራር አባልና የኦሮምያ ክልል ፕሬዚዳንት አቶ ሽመልስ አብዲሳ ከ8ወራት በፊት የተናገሩት ነው የተባለና ሾልኮ የወጣ አንድ ንግግር ሰሞኑን በማኅበራዊ መገናኛ ብዙሃን ተለቋል፡፡
አወዛጋቢና አነጋጋሪ ነው የተባለው የአቶ ሽመልስ አብዲሳን ንግግር የብልፅግና ፓርቲን በአመራርነት የያዙ ባለሥልጣናት አቋም የሚጋሩት ይሆን? የሚል ጥያቄ አስነስቷል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በዛሬው ዕለት በባህር ዳር ስለጉዳዩ በሰጡት ምላሽ የአቶ ሽመልስ ንግግር ስህተት መሆኑን ጠቅሰው አቶ ሽመልስ አስተያየት ሊገመገም እንደሚገባው መናገራቸውን ቃል አቀባያቸው አቶ ንጉሡ ጥላሁን ማስታወቃቸው ተነግሯል፡፡
በዚህ ጉዳይ ላይ በወቅቱ ምላሽ እንዲሰጡን በተደጋጋሚ የጠየቅናቸው የፖርቲና የመንግሥት ባለሥልጣናት ፈቃደኛ ሳይሆኑ ቢቀሩም የኦሮምያ ክልላዊ መንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ቢሮ ኃላፊ አቶ ጌታቸው ባልቻ ንግግሩን ያልሰሙት በመሆኑ አስተያየት ለመስጠት እንደሚቸገሩ፣ ወደፊት ሁኔታውን አጣርተው እንደሚመለሱ ገልጠውልናል፡፡ የአቶ ሽመልስን ንግግር ያደመጡና አሰተያየታቸውን በማኅበራዊ ሚዲያ ከገለጹት መካከል አቶ ግዛው ለገሠ አንዱ ናቸው፡፡ በዋሽንግተን ዲሲ አካባቢ ነዋሪና የአይቲ ባለሙያ የሆኑት አቶ ግዛው በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ ከኢህአፓ ጊዜ ጀምሮ ተሳታፊ የነበሩና በተለያዩ የሚድያ ዘርፎችም አስተያየታቸውን በመግለጽ ይታወቃሉ፤ አነጋግረናቸዋል፡፡
ዝርዝሩን ከተያያዘው የድምፅ ፋይል ያዳምጡ።
Your browser doesn’t support HTML5