ምግብን እንደ ጦር መሣሪያ የሚጠቀሙ ኃይሎችን ዩናይትድ ስቴትስ በተጠያቂነት እንድትይዝ የሚያሳስብ የውሣኔ ሃሳብ የህግ መወሰኛ ምክር ቤቷ የውጭ ጉዳዮች ኮሚቴ አሳለፈ።
ለምግብ ዋስትና መጥፋት ዋናው ምክንያት ግጭት መሆኑን የኮሚቴው አባላት ከመነሻቸው ጠቁመዋል።
ኮሚቴው ትናንት ያሳለፈውን የሁለቱንም ፓርቲዎች ድጋፍ ያገኘው የውሣኔ ሃሳብ የተረቀቀውና የተመከረበት በሪፐብሊካኑ የአይዳሆ፣ የኦሬገን፣ የኢንዲያና የደቡብ ዳኮታ እንደራሴዎች ጂም ራይሽ፣ ጄፍ መርክሊ፣ ቶድ ያንግ እና ጃን ትዩን፤ እንዲሁም በዴሞክራቶቹ ኮሪ ቡከር እና ባብ ሜኔንዴዝ ነው።
የሌሎች ባልደረቦቻቸውን ሃሳብ የተቀላቀሉት የኮሚቴው አጋር መሪ ሴናተር ራይሽ ባሰፈሩት መልዕክት፣ “ኢትዮጵያ፣ ደቡብ ሱዳን፣ ሶሪያና የመን ውስጥ እየተዋጉ ያሉ ኃይሎች የግብርና ግብዓቶችና ውጤቶችንና መዋቅሮችን ሆን ብለው እንደሚያወድሙ፣ ገበያውን መረጋጋት እንደሚያሳጡ፣ በሰብዓዊ አቅርቦት ተቋማትና ሠራተኞች ላይ የፀጥታና የአሠራር መደናቅፎችን እንደሚደቅኑ” ተናግረዋል።
“በዚህም በሲቪሎች ላይ ታልሞ የተቀነባበረ የረሃብ ቸነፈር ያደርሳሉ” ብለዋል ራይሽ።
ሩሲያንም “በዓለም ላይ የበረታ ረሃብን በመዝራት ዘመቻ” ከስሰዋል።
የሴኔቱ ኮሚቴ ያሳለፈው የውሣኔ ሃሳብ ረሃብን ሆን ብሎ እንደ ጦር መሣሪያ መጠቀምን አውግዞ የዩናይትድ ስቴትስ መንግሥትና አጋሮቿም የአድራጎቱን አቀናባሪዎች ፈጥነው በተጠያቂነት እንዲይዙ ጠይቋል።
“የምግብ እርዳታ፤ አቅርቦቱ በብርቱ የሚያስፈልጋቸውን ሲቪሎች ለመጉዳት ጉዳይ አለመዋሉን ለማረጋገጥ ያሉንን መሣሪያዎች ሁሉ መጠቀም አለብን” ሴናተር ራይሽ ባሰፈሩት ሃሳባቸው።
ሌሎቹም እንደራሴዎች ተደጋጋፊና ተመሳሳይ መልክዕክቶችን አስፍረዋል።