የዩናይትድ ስቴትስ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንተኒ ብሊንክን የሱዳን ጠቅላይ ሚኒስትር አብደላ ሃምዶክን በስልክ አነጋገሩ።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ኔድ ፕራይስ ባወጡት መግለጫ እንዳስታወቁት ትናንት ሚኒስትር ብሊንክን ከሱዳን ጠቅላይ ሚኒስትር ሃምዶክ ጋር በኢትዮጵያ የአማራ ክልል እና የአፋር ክልል ወታደራዊ ፍጥጫ እየተስፋፋ መሆኑ፣ በትግራይ ክልል ያለው ሰብዓዊ ሁኔታ እያሽቆለቆለ መሆኑ እና የኤርትራ ወታደሮች ተመልሰው ወደትግራይ ክልል እየገቡ ነው በሚሉ ሪፖርቶች ዙሪያ ሃገሮቻቸው ያላቸውን የጋራ ስጋት አንስተው ተወያይተዋል።
የተጠቀሱት ጉዳዮች በቀጣናው መረጋጋት ላይ ተጽዕኖ የሚያሳድሩ እንደሆኑም ገልጸዋል።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ብሊንክን እና የሱዳን ጠቅላይ ሚኒስትር ሃምዶክ ሁሉም ወገኖች ወደተኩስ አቁም የሚያመራ ድርድር እንዲያካሂዱ፣ የኢትዮጵያን አንድነት እና ሉዓላዊነት ለማስጠበቅ አሳታፊ የፖለቲካ ንግግር እንዲያደርጉ እንዲሁም ችግር ላይ ላሉ ሰዎች የተሟላ የሰብዓዊ ረድዔት ተደራሽነት እንዲፈቀድ ለማበረታታት መስማማታቸውን የቃል አቀባዩ መግለጫ አመልክቷል።
የውጭ ጉዳይ ሚንስትሩ እና ጠቅላይ ሚንስትሩ ስለሱዳን የዲሞክራሲ ሽግግር ርምጃ እንዲሁም የሃገሮቻቸውን ግንኙነቶች ማስፋትን አምስመልክተው ተወያይተዋል።