በምዕራብ እና መካከለኛው አፍሪካ ጉብኝት በማድረግ ላይ የሚገኙት የአሜሪካው የውጪ ጉዳይ ሚኒስትር አንተኒ ብሊንከን፣ በአቢጃን፣ አይቮሪ ኮስት በተሰናዳና በምግብ ዋስትና እና የኢኮኖሚ ዕድገት ላይ ባተኮረ ጉባኤ እና አውደ ርዕይ ላይ ተገኝተዋል፡፡
“አፍሪካ ራይስ” በተሰኘና በሩዝ ላይ ምርምር በሚያደርግ ተቋም ዋና መሥሪያ ቤት ውስጥ በተዘጋጀው ጉባኤ ላይ ብሊንከን ባደረጉት ንግግር፣ በሥፍራው በመካሄድ ላይ ያለውን ሥራ እንደታዘቡት፣ አፍሪካ ራሷን ብቻ ሳይሆን፣ ዓለምንም መመገብ ትችላለች የሚለውን እና ከዚህ በፊት ፕሬዝደንት ባይደን የተናገሩትን በመጥቀስ፣ “ያንን ማድረግ የማይቻል ነገር አይደለም” ሲሉ ተደምጠዋል።
SEE ALSO: ብሊንከን የአፍሪካ ዋንጫ ጨዋታ ላይ ተገኙዘላቂነት ያለው ምርት በተከታታይ ለማግኘት የአፍሪካ ልማት ባንክ የአየር ንብረት ለውጥን የሚቋቋሙ የሰብል ዝርያዎችን ለመፍጠር የሚያደርገውን ጥረት ያደነቁት ብሊንከን፣ የተመጣጠነ ምግብን በማምረት እና ምርቱንም ለማሰራጨት በሚያስፈልገው መሠረተ ልማት ግንባታ ላይ በተቋሙ የተሠራውን ምርምር አድንቀዋል።
ለዓለም ምግብ ፕሮግራም ከፍተኛውን ርዳታ በማድረግ አገራቸው ትልቅ ድርሻ እንዳላት ያወሱት ብሊንከን፣ በአፍሪካ የሚገኙ ሚኒስትሮች አሜሪካ ለምታደርገው ልገሳ ምስጋናቸው ላቅ ያለ መሆኑን እንደነገሯቸው አመልክተዋል።
በአፍሪካ የሚገኙ የተመጣጠነ ምግብን ሊሰጡ የሚቹ ሰብሎችን፣ የአየር ንብረት ለውጥን እንዲቋቋሙ በምርምር እንዲታገዙ ማድረግ ለአፍሪካ እጅግ ጠቃሚ መሆኑን ያወሱት የውጪ ጉዳይ ሚኒስትሩ፣ በዚህ ረገድ የአሜሪካ ዓለም አቀፍ ልማት ድርጅት (ዩኤሴይድ) በአፈር እና ሰብል ምርምር ላይ የሚያደርገው አስተዋጽዎ ጉልህ እንደሆነ ተናግረዋል።