የጎርፍ አደጋ ደቡብ ሱዳንን ማወኩ ቀጥሏል

በምስራቃዊው ሱዳን ከባድ ጎርፍ ምክንያት የፈራረሱ መኖሪያ ቤቶች

በደቡብ ሱዳን በተደጋጋሚ በመከሰት ላይ ባለው የጎርፍ አደጋ 893ሺሕ የሚሆኑ ሰዎች ችግር ላይ መውደቃቸውንና ከ241ቪሕ በላይ የሚሆኑት ደግሞ መፈናቀላቸውን የተመድ የሰብዓዊ ጉዳዮች ማስተብባበሪያ ቢሮ (ኦቻ) አስታውቋል።

ለአየር ንብረት ለውጥ በከፍተኛ ደረጃ ተጋላጭ የሆነችው ደቡብ ሱዳን ለአስርተ ዓመታት ያልታየ የጎርፍ አደጋ እንደገጠማት የረድኤት ድርጅቶች ሲያስጠነቅቁ ሰንብተዋል።

“ጎርፍ በመላ ሃገሪቱ ተፈናቃዮችን አደጋ ላይ መጣሉን ቀጥሏል” ብሏል ኦቻ ባወጣው መግለጫ።

ከፍተኛ ዝናብና ጎርፍ 15 የመተላለፊያ መንገዶችን በመዝጋቱ ወደ ሕዝቡ ለመድረስ አስቸጋሪ እንደሆነ ቢሮው አስታውቋል።

በደቡብ ሱዳን ከሚገኙት 78 አውራጃዎች ውስጥ በ42 አውራጃዎች የሚገኙ ሰዎች በጎርፍፉ ምክንያት ሕይወታቸው ሊመሳቀል እንደቻለም ታውቋል።

በእ.አ.አ 2011 ነጻነቷን የተቀዳጀችውና በዓለም ወጣቷ ሃገር የሆነችው ደቡብ ሱዳን፤ አለመረጋጋት፣ ሁከት፣ የኢኮኖሚ ድቀት እንዲሁም እንደ ድርቅና ጎርፍ የመሰሉ የተፈጥሮ አደጋዎች ሲያውኳት ከርሟል።