ሩዋንዳ ከአንድ የአሜሪካ የኑክሌር ኩባንያ ጋራ ስምምነት ተፈራረመች

ፎቶ ፋይል፡- ኪጋሊ፣ ሩዋንዳ.

ሩዋንዳ አነስተኛ የኑክሌር ማብላሊያዎችን ለመገንባት የሚያስችል የመግባቢያ ስምምነት ከአንድ የአሜሪካ የኑክሌር ኩባንያ ጋራ ተፈራርማለች፡፡

13 ሚሊዮን ሕዝብ ያላት ሩዋንዳ የኤሌክትሪክ ኃይሏን ከውሃ እና ከሌሎችም ምንጮች የምታገኝ ሲሆን፣ የወጠነችው ሲቪል የኑክሌር ፕሮራም የኤሌክትሪክ ኃይሏን አስተማማኝና ተደራሽ ለማድርግ ይረዳታል ተብሏል።

ናኖ ኑክሌር ኢነርጂ የተሰኘው የአሜሪካው የኑክሌር ኩባንያ ማብላሊያዎቹን ከመገንባት በተጨማሪ የቴክኒክና የሥልጠና እገዛ እንደሚያደርግም ታውቋል። ግንባታው በመጪዎቹ ጥቂት ዓመታት ውስጥ እንደሚካሄድ ተጠቁሟል።

ከአሜሪካ ጋራ የተፈረመው የመግባቢያ ስምምነት፣ በተመሳሳይ የጀርመን እና ካናዳ ጥምር ከሆነ ኩባንያ ጋራ አነስተኛ የኑክሌር ማብላሊያ ለማቋቋም የተፈረመውን ስምምነት ተከትሎ መምጣቱን የኤኤፍፒ ዘገባ አመልክቷል።