የሩዋንዳው ፕሬዝዳንት ፖል ካጋሜ ሁለት ዕጩዎች ብቻ ተፎካካሪያቸው ሆነው እንዲቀርቡ በተደረገበት ምርጫ ከፊል ውጤት ከመራጩ ሕዝብ 99 ነጥብ 15 በመቶ የሆነ ድምጽ በማግኘት ያችን አገር ለአራተኛ የሥልጣን ዘመን ለመምራት እየተሰናዱ ነው። ትንሽቱን አፍሪቃዊት ሃገር ለሦስት አስርት ዓመታት በጠንካራ ክንድ በፕሬዚዳንትነት ያስተዳደሩት ካጋሜ በትላንቱ ምርጫ የማሸነፋቸው እጣ ያልተጠበቀ አልነበረም።
የምርጫ ጣቢያዎች ከተዘጉ ሰባት ሰዓታት በኋላ የሃገሪቱ የምርጫ ኮምሽን ያወጣው ከፊል የምርጫ ውጤት 99 ነጥብ 15 በመቶ ድምጽ ማግኘታቸውን ይፋ አድርጓል። ያሁኑ ውጤት የ98 ነጥብ 79 በመቶውን መራጭ ድምጽ ካገኙበት ከሰባት ዓመታት በፊት በተካሄደው ምርጫ ከነበረውም የላቀ መሆኑም ተመክቷል። እስካሁን ተጠናቆ ከገባው 79 በመቶው የመራጭ ድምጽ፣ የዴሞክራቱ ግሪን ፓርቲ እጩው ፍራንክ ሃቢኔዛ የ0 ነጥብ 53 በመቶ ሲያገኙ፤ በግል የተወዳደሩት ፊሊፕ ምፓይማና ደግሞ የ0 ነጥብ 32 በመቶ ብቻ ማግኘታቸውን ይፋ የተደረገው ውጤት አመልክቷል።
የከፊል ምርጫው ውጤት ይፋ መደረጉን ተከትሎም የ66 አመቱ ካጋሜ ከፓርቲያቸው የሩዋንዳ አርበኞች ግንባር (RPF) ዋና ፅህፈት ቤት ሆነው ባሰሙት ንግግር ለተጨማሪ አምስት አመታት የስልጣን ዘመናቸውን ያራዘሙላቸውን ሩዋንዳውያን አመስግነዋል።
"የምርጫው ውጤቶች በጣም ከፍተኛ ነጥብ የሚያመለክቱ አሃዞች ብቻ አይደሉም። መቶ በመቶ የሆነ ውጤት ቢሆንም ስለ ቁጥር ብቻ አይደለም። ይልቁንም ሕዝቡ ያለውን እምነት የሚያሳይ እንጂ! ያ ነው በጣም አስፈላጊው ጉዳይ!" ብለዋል።
“ሁሉንም ችግሮች በጋራ መፍታት እንደምንችል ተስፋ አለኝ” ሲሉም እምነታቸውን አንጸባርቀዋል።