ሩሲያ ዩክሬን ውስጥ በሚሳይል ስድስት ሰዎች ገደለች

  • ቪኦኤ ዜና

ሩሲያ ዩክሬን ውስጥ በሚሳይል ስድስት ሰዎች ገደለች

ሩሲያ ዛሬ ሐሙስ በበርካታ የዩክሬን አካባቢዎች ላይ የሚሳይል ጥቃት ማድረሷን የዩክሬን ባለሥልጣናት ተናገሩ፡፡

ሩሲያ ከተኮሰቻቸው 81 ሚሳይሎች መካከል 34ቱን እና የሩሲያ ባለሥልጣናት የተጠቀሙባቸውን አራት ድሮኖች መትቶ መጣሉን የዩክሬን የጦር ኃይል አስታውቋል፡፡ የዩክሬን ፕሬዚዳንት ቮሎዶሚር ዜሌንስኪ ባስተላለፉት መልዕክት “ወራሪዎቹ ሊያሸብሩ የሚችሉት ሲቪሉን ህዝብ ብቻ ነው፡፡ እሱ ግን አይጠቅማቸውም፡፡ ባደረጉት ሁሉ መጠየቅ አይቀርላቸውም” ብለዋል፡፡

የምዕራባዊ ልቪቭ ክፍለ ግዛት አገረ ገዢ በበኩላቸው ሩሲያ መኖሪያ አካባቢ ላይ በተኮሰችው ሚሳይል አምስት ሰዎች መግደሏን ገልጸዋል፡፡

ድኒፕሮፔትሮቭስክ ውስጥ ደግሞ አንድ ሰው ሲገደል ሌሎች ሁለት ሰዎች መቁሰላቸውን ባለሥልጣናቱ አስታውቀዋል፡፡ ኦዴሳ ክፍለ ሀገር ኪየቭ እና ኻህርኺቭ ውስጥም ጥቃት መድረሱ ተገልጿል፡፡

የዛሬው የሩሲያ ጥቃት የዛፖሮሮዢያ የኒውክሊየር ኃይል ጣቢያን የኤሌክትሪክ መስመር እንዳቋረጠው ተዘግቧል፡፡ የዓለም አቀፍ የአቶሚክ ኃይል ድርጅት ዋና ዳይሬክተር ራፋኤል ግሮሲ ሩሲያ ዩክሬንን ከወረረች ወዲህ የኒውክሌር ጣቢያው የኤሌክትሪክ አቅርቦት ስድስት ጊዜ መቋረጡን ጠቅሰው አስቸኳይ ዕርምጃ እንዲወሰድ አሳስበዋል፡፡ “የማየው ቸልተኝነት አስደንግጦኛል” ብለዋል፡፡

አውሮፓ ካሉት ሁሉ ትልቁ በሆነው የዛፖሮዢዢያው የኒውክሊየር ኃይል ጣቢያ አጠገብ ሩሲያ በተደጋጋሚ ጥቃት ማድረ ስጋት ፈጥሯል፡፡

ይህ በእንዲህ እንዳለ የዩክሬን ፕሬዚደንት ቮሎዶሚር ዜሌንስኪ የዩናይትድ ስቴትስ ኮንግሬስ የተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ኪየቭን እንዲጎበኙ ጋበዙ፡፡

ኪየቭ አፈ ጉባኤ ኬቭን መካርቲን የጋበዟቸው ትናንት ረቡዕ ለሲ ኤን ኤን ቴሌቭዥን በሰጡት ቃል መጠይቅ ላይ ነው፡፡

“ሚስተር መካርቲ ይምጡና ምን የሚደረገውን ይዩ በጦርነቱ ምን እንደደረሰብን ማን እየተዋጋ እንደሆን ይመልከቱ እና ከዚያ በኋላ አቋም ይያዙ”ብለዋል፡፡

የምክር ቤት አፈ ጉባኤ ምካርቲ በበኩላቸው ስለጉዳዩ ለመረዳት ኪቭ መሄድ የለብኝም መረጃዎቼን በሚሰጡ ገለጻዎችም በሌላም መንገድ አገኛለሁ” ሲሉ ምላሽ ሰጥተዋል፡፡