ሩሲያ 92 የዩክሬን ድሮኖችን መደምሰሷን አስታወቀች

  • ቪኦኤ ዜና

የሩስያ ወታደሮች የውጊያ ስልጠና ላይ

የሩሲያ የመከላከያ ሚኒስቴር በሩሲያ እና ዩክሬን ድንበር አካባቢ ያሉ ኢላማዎች ላይ ያነጣጠሩ 92 የዩክሬን ሰው አልባ አውሮፕላኖችን (ድሮኖችን) የአየር መከላከያችን መትቶ ጥሏል ሲል አስታወቀ፡፡

“ከግማሽ የሚበልጡት ድሮኖች በክራስኖዶር አየር ላይ ሲመቱ፣ ፍርስራሾቹ በርካታ ቤቶች ላይ ወድቀዋል” ያለው ሚኒስቴሩ ይሁን እንጂ “ምንም ጉዳት አላደረሱም” ብሏል፡፡

የሩሲያ የአየር መከላከያዎች በኩርስክ ፣ ሮስቶቭ ፣ ብራያንስክ ፣ ቤልጎሮድ ፣ ቮሮኔዝ ፣ የአዞቭ ባህር እና ሩሲያ በኃይል በያዘችው ክሬሚያ ላይ በርካታ ድሮኖችን መትተው መጣላቸውን ሚኒስቴሩ አስታውቋል።

የዩክሬን ጦር ኃይል በበኩሉ በቼርካሲ፣ ዲኒፕሮፔትሮቭስክ፣ ዶኔትስክ፣ ኬርሰን፣ ኪቭ፣ ሚኮላይቭ ፣ ኦዴሳ ፣ ፖልታቫ ፣ ሱሚ እና ዛፖርዥዥያ ክልሎች በአንድ ሌሊት ከተሰማሩ 62 የሩሲያ ድርኖች መካከል 41ዱን መትተው መጣላቸውን ገልጿል፡፡

በዛፖርዥዥያ እና በአንዳንድ የዩክሬን ግዛቶች የሩሲያ ድሮኖች በጋዝ ማስተላለፊያ ባንቧዎችና መኖሪያ ቤቶች ላይ ጉዳት ማድረሳቸውን ሰዎችንም ማቁሰላቸው ተነግሯል፡፡

የዩክሬን ፕሬዝዳንት ቮሎዲሚር ዜሌንስኪ ከፈረንሳይ ፕሬዝዳንት ኢማኑዌል ማክሮን ጋር ለመነጋገር ወደ ፓሪስ ከማቅናታቸው በፊት ከጠቅላይ ሚኒስትር ኬይር ስታርመር እና የኔቶ ዋና ፀሀፊ ማርክ ሩት ጋር ለመገናኘት ብሪታንያ ገብተዋል።

ፈረንሣይ ለዩክሬን ለረዥም ጊዜ ድጋፏን እንደምትቀጥል አረጋግጣ ከለገሠቻቸው ወታደራዊ መሣሪያዎች በተጨማሪ 2300 የኪየቭ ብርጌድ ወታደሮችን እያሰለጠነች ነው፡፡ ዩክሬን ውስጥ ሌሎች 2200 የሚሆኑ ወታደሮችን ማሰልጠኗም ተመልክቷል፡፡