ሩሲያ ባደረሰችው ብዛት ያለው የሚሳይል እና የድሮን ጥቃት ከዩክሬን ትላልቅ የኃይል ማመንጫዎች አንደኛውን ማውደሙን እና ሌሎችየኅይል ማመንጫዎች ላይ ጉዳት ማድረሱን የሀገሪቱ ባለሥልጣናት ትላንት ሐሙስ ገለፁ።
ጥቃቱ “ሩስያ የኃይል መሠረተ ልማቶችን ኢላማ በማድረግ እንደገና የተያያዘችው የጥቃት ዘመቻ አካል ነው” ብለዋል፡፡
ለኪየቭ፣ ቸርካሲ እና ዛይቶሚር ግዛቶች ዋናው የኃይል አቅርቦት ማከፋፈያ የሆነው ትሪፒልስካ ተቋም በተደጋጋሚ ተደብድቧል፡፡ በድብደባው ኃይል ማስተላለፊያዎች (ትራንስፎርመሮች)፣ ሞተሮችና፣ ጀኔሬተሮች በእሳት ተቃጥለው ወድመዋል፡፡
ጥቃቱን ካደረሱት መካከል የመጀመሪያው ሰው አልባ አውሮፕላን (ድሮን) ሲቃረብ ሠራተኞቹ ህይወታቸውን ለማዳን በመጠለያ ውስጥ መሸሸጋቸውን የፋብሪካው አስተዳዳሪ የመንግሥት ኩባንያ የቁጥጥር ቦርድ ሰብሳቢ አንድሪ ጎታ ተናግረዋል።
በሞስኮ ንግግር ያደረጉት የሩስያው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን ጥቃቱ “ዩክሬን የሩሲያ ነዳጅ ዘይት ማጣሪዎችን ኢላማ አድርጋ ላደረሰቸው ጥቃት የተሰጠ ምላሽ ነው” ብለዋል፡፡
ሩስያ የኃይል መሠረተ ልማቶችን ኢላማ በማድረግ እንደገና የተያያዘችው የጥቃት ዘመቻ አካል ነው”
ትሪፒልስካ ለ3 ሚሊዮን ደንበኞች የኤሌክትሪክ ኃይል የሚያቀርብ ቢሆንም የኃይል መቋረጥ አላስከተለም፡፡ በዚህ ወቅት ክፍለ ጊዜ የሚኖረው የኤሌክትሪክ ፍላጎት አነስተኛ በመሆኑ ለማብቃቃት ችሏል፡፡
የበጋው ወቅት ሲገባ ግን የአየር ማቀዝቀዥዎች አጠቃቀም ስለሚጨምር በጥቃቱ የደረሰው ጉዳት እያደር ሊሰማ እንደሚችል ተመልክቷል፡፡
በዩክሬን ሁለተኛዋ ትልቅ ከተማ በሆነችው በካርኪቭ በአንድ ሌሊት የተፈፀሙ ቢያንስ 10 ሌሎች ጥቃቶች የኃይል መሠረተ ልማቶችን ጎድተዋል።
የዩክሬን ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዲሚትሮ ኩሌባ “በተደጋጋሚ በተከሰተው ጥቃት በክልሉ ከ 200 000 በላይ ሰዎች የኤሌክትሪክ ኃይል ተቋርጦባቸዋል” ብለዋል፡፡
ሩሲያ በቅርቡ በዩክሬን የኃይል ማመንጫዎች ላይ የምታካሂደውን ጥቃት እንደገና ቀጥላለች፡፡ ባለፈው ወር ያደረሰችው ጥቃት ብዛት ያላቸውን የአገሪቱን አካባቢዎች አጨልመዋል ፡፡ እ ኤ አ በ 2022 ወረራው ከጀመረበት ጊዜ ወዲህ ዩክሬን በዚህ ደረጃ ስትጨልም ይህ የመጀመሪያው ጊዜ መሆኑም ተመልክቷል፡፡