የዩክሬን ፕሬዝዳንት ቮሎዲሚር ዜለንስኪ ዩክሬን ወደ ሩሲያ ኩርስክ ክልል ዘልቃ በመግባት ለሁለት ሳምንታት በሚጠጋ ጊዜ ባካሄደችው ጥቃት ግቧን እያሳካች መሆኑን አስታውቀዋል፡፡
ተጨማሪ የሩሲያ ጥቃቶች እና ወታደራዊ እንቅስቃሴዎችን ለመከላከል ነጻ የመከላከያ ቀጠና እየፈጠረች መሆኑም ዜለነስኪ ተናግረዋል፡፡
ኪቭ ወታደሮችዋን የሩሲያን ድንበር ተሻግረው እንዲገቡ ያደረገችው እኤአ ነሀሴ 6 በሰነዘረችው ድንገተኛ ጥቃት ነው፡፡
ሞስኮ እኤአ የካቲት 2022 ዩክሬንን ላይ ሙሉ ወረራ ማካሄድ ከጀመረች ጊዜ አንስቶ ዩክሬን እንዲህ ዓይነቱን ትልቅ ጥቃት ያካሄደቸው ለመጀመሪያ ጊዜ ነው፡፡
ጥቃቱ ሞስኮ ወደፊት በማንኛውም የሰላም ድርድር ላይ ፍትሃዊ በሆነ መንገድ እንድትደራደር ጫና ለማድረግ የታለመ ነው፡፡ የሰላም ድርድሩ ስለመደረጉ ግን እስካሁን የተገለጸ ነገር የለም፡፡
የዩክሬን ወታደሮች በምስራቅ የሀገሪቱ አካባቢዎች በሚገኘው ግንባር የሩሲያን ጦር ለመቀቋቋም እየታገሉ ቢሆንም፣ ከኩርስክ ክልል ባካሄደችው ጥቃት በመቶዎች የሚቆጠሩ የሩሲያ ወታደሮችን መያዝዋን ግን ዩክሬን አስታውቃለች፡፡
በምስራቃዊ ዩክሬን በተለይም በዶኔትስክ ግዛት የሩሲያ ወታደሮች የፖክሮቭስክ ከተማን ለመያዝ በፍጥነት እየገሰገሱ ነው፡፡ ከወራት ሙከራ በኋላ አሁን ከከተማዪቱ ደጃፍ 10 ኪሎ ሜትሮች ላይ እንደሚገኙም ተነገሯል፡፡
የዩክሬን ባለስልጣናት ነዋሪዎች በበተለይም ልጆች ያሏቸው ቤተሰቦች ለደህንነታቸው ሲሉ በአስቸኳይ ፖክሮቭስክንና በአቅራቢያው የሚገኙ ከተሞችን በመልቀቅ እንዲወጡ አሳስበዋል፡፡
በፖክሮቭስክ አካባቢ ከባድ ጦርነቶች አሁንም እየተካሄዱ ሲሆን የዩክሬን ተከላካዮች በሩሲያ መድፍ፣ ሚሳይሎች እና ቦምቦች ከወደሙት አካባቢዎች እያፈገፈጉ ነው።
ፖክሮቭስክ በዶኔትስክ ክልል ውስጥ የዩክሬን ቁልፍ የመከላከያ ምሽግ እና የሎጂስቲክስ ማዕከል ናት፡፡ ይህን ስፍራ መልቀቅ የዩክሬንን የመከላከል አቅም በእጅጉ እንደሚጎዳ ተመልክቷል፡፡
ይህ በእንዲህ እንዳለ ሩሲያ በቅርቡ በዩክሬን ዋና ከተማ ላይ የባላስቲክ ሚሳኤል ጥቃት መፈጸሟን ተከትሎ በኪቭ አቅራቢያ የሚገኙ የዩክሬን አየር መከላከያ ክፍሎች የሩሲያ የአየር ጥቃትን ለመመከት እየሰሩ ነው።
ሩሲያ ትላንት እሁድ ማለዳ ላይ ስምንት ሚሳዬሎችን ወደ ዩክሬን ስታስወነጭፍ ከነዚህም መካከል ዩክሬን አምስቱን በተሳካ ሁኔታ ጥላለች ሲሉ የዩክሬን አየር ሃይል አዛዥ ተናግረዋል፡፡