በምስራቅ ኡክራይን ላይ በተከፈተ ተኩስ አራት የኡክራይን ወታደሮች በመገደላቸው የሀገሪቱ ፕሬዚዳንት ቮሎዲሚር ዘለንስኪ ከሩስያው ፕሬዚዳንት ቭላዲሚር ፑቲን ጋር በስልክ መነጋገራቸውን ገልፀዋል።
ዋሺንግተን ዲሲ —
"ወድያውኑ ነው ስልክ የደወልኩላቸው፤ ይህ ወደ ሰላም ሊያቀርበን አይችልም አልኳቸው" ሲሉ ዘለንስኪ ዛሬ ኪቭ በተደረገ ጋዜጣዊ ጉባዔ ተናግረዋል። በሞስኮ የሚደገፉት ተገንጣዮች "ህዝባችንን መግደል እንዲያቆሙ" እንዲነግሯቸው ለፑቲን ጥሪ አድርጊያለሁ ሲሉም አክለዋል።
ፑቲን የገቡላቸው ቃል እንዳለና ቆይቶ የሚገልጽ መሆኑን የኡክራይኑ ፕሬዚዳንት ገልፀዋል። ሞስኮ ስለተባለው የስልክ ጥሪ የተናገረቸው ነገር የለም።
የኡክራይን የመከላከያ ሚኒስቴር ባወጣው መግልጫ መሰረት ተገንጣዮቹ ትላንት በዶኔትስክ ክልል በሚገኘው ወታደራዊ ሰፈር ላይ ተኩስ ከፍተዋል። ፈንጂ ተኳሾችን፣ መትረየሶችንና ጠመንጃዎችን ተጠቅመው እንደተኮሱ የመከላከያው ሚኒስቴር ገልጿል።