የዓረብ ሊግ የባሻር አል አሳድን ሦሪያ እንደገና በአባልነት እንዲቀበል ሩሲያ ማግባባት ይዛለች ሲሉ በአካባቢው የተመደቡ ዲፕሎማቶች ተናገሩ።
ዋሺንግተን ዲሲ —
የአሳድ አስተዳደር በፍጥነት ሕጋዊ ዕውቅና እንዲያገኝ ክሬምሊን በጉጉት የሚጠብቀው፣ በጦርነት የዳሸቀችውን ሦሪያ መልሶ ለመገንባት የሚያስችል ገንዘብ ለማሰባሰብና ፕሬዚዳንቱ በሥልጣን እንዲቆዩ ተስፋ በማድረግ ነው።
የክሬምሊን ቤተ መንግሥት ዓላማ የዓረብ ሊግ በመጪው ወር ቲኒዝ ውስጥ የመሪዎች ጉባዔ ሲያካሂድ ግብጽ፣ የዓረብ ኤሚሬቶች፣ ኢራቅና ሳዑዲ ዓረቢያ ለሦሪያ ዳግም በሊጉ መግባት ድጋፍ እንዲሰጡ ነው።
የሦሪያ እንደገና ወደ ሊጉ መመለስ፣ አለመመለስ ጉዳይ በቱኒዙ የመሪዎች ጉባዔ አጀንዳ ውስጥ ባይኖርም የሩሲያ ዲፕሎማቶች ግን ከመጋረጃው ጀርባ ሆነው የዓረብ ሸሪኮቻቸውን በመወትወት ላይ ናቸው ተብሏል።
22 የዓረብ ሃገሮችን በአባልነት ያቀፈው ሊግ እአአ በ2011 ሦሪያን ያስወጣው የአሳድ መንግሥት በሱኒ ሙስሊሞች የተመራውን ህዝባዊ ተቃውሞ ለመጨፍለቅ የወሰደውን ጨካኝ ዕርምጃ ተከትሎ ነው።
የአሳድን አረመኔአዊ ዕርምጃ በመቃወም፣ በርካት የዓረብ ሃገሮች አምባሳደሮቻቸውን ከደማስቆ መጥራታቸውም ይታወሳል።