ፕሬዝደንት ቭላድሚር ፑቲን የሩሲያ ኅይሎች በዩክሬን ጦርነት ዋና ግባቸውን ለመምታት እየተቃረቡ መኾኑን በዓመታዊ ጋዜጣዊ መግለጫቸው ላይ ተናግረዋል።
በጦር ሜዳው እንዳገኙ ለሚገልጹት የበላይነት አዲሶቹ የሩሲያ ሱፐርሶኒክ ሚሳዬሎች አስተዋጽኦ እንዳደረጉ አመልክተዋል።
በመንግሥት ቴሌቭዥን ቀርበው ከሩሲያውያን ለቀረቡላቸው ጥያቄዎች መልስ የሰጡት ፑቲን፣ የሀገራቸው ኅይሎች በሁሉም ግንባሮች ግሥጋሤ እያደረጉ መሆኑን ተናግረዋል።
ፑቲን ፣ “ሁኔታዎች እየተቀያየሩ ነው። በየቀኑ በሁሉም ግንባሮች ግሥጋሤ አለ” ሲሉ አስታውቀዋል።
ሩሲያ በምሥራቅ ዩክሬን እ.አ.አ ከ2022 ወዲህ በፍጥነት እየገሠገሠችና በርካታ ሥፍራዎችን በመቆጣጠር ስትራቴጂካዊ ጠቀሜታ ወዳላቸው ከተሞች በመቃረብ ላይ መኾኗን ምዕራባውያንና የሩሲያ ወታደራዊ ተንታኞች በመግለጽ ላይ ናቸው።
ዩክሬን የሩሲያን ኩርስክ ክልል ይዛ መቆየቷን በተመለከተ ለቀረበላቸው ጥያቄ ሲመልሱም፣ የዩክሬን ኅይሎች “በእርግጠኝነት እንዲወጡ የደረጋል” ሲሉ ተደምጠዋል።
የሩሲያ አዲስ ሱፐርሶኒክ ‘ኦረሽኒክ’ ሚሳዬሎች ከእይታ ውጪ ስለኾኑ መትቶ ለመጣል እንደማይቻል ፑቲን ተናግረዋል። ሩሲያ የሠራቻቸውን እነዚህ ሚሳዬሎች የዩክሬን ወታደራዊ ፋብሪካዎችን በመምታት ሞክራቸዋለች፡፡ በእነዚህ ሚሳዬሎች ተጨማሪ ድብደባዎችን እንደሚያደርጉና የምዕራባውያን የመከላከያ መሣሪያዎች መትተው ይጥሏቸው እንደሁ የሚታይ ይሆናል ብለዋል ፑቲን።