ሩሲያ ከዓለም አቀፉ የጠፈር ጣቢያ እየወጣች ነው

  • ቪኦኤ ዜና
ፎቶ ፋይል፦ ወደ ዓለም አቀፉ የጠፈር ጣቢያ ያቀኑት የሩሲያ ኮስሞናውቶች

ፎቶ ፋይል፦ ወደ ዓለም አቀፉ የጠፈር ጣቢያ ያቀኑት የሩሲያ ኮስሞናውቶች

ሩሲያ እኤአ በ2024 ከዓለም አቀፉ የጠፈር ምርምር ጣቢያ እንደምትወጣና በምድር ምህዋር ላይ የራሷን የጠፈር ምርምር ጣቢያ እንደምትገነባ አስታወቀች።

ይህ የተገለፀው የአገሪቱ የጠፈር ምርምር ሥራ አስፈፃሚ ዩሪ ባሪሶቭ ትናንት ማክሰኞ ከፕሬዚዳንት ቭላዲሚር ፑቲን ጋር በተገናኙበት ወቅት ነው።

“ሩሲያ ዓለም አቀፉን የጠፈር ምርምር ጣቢያ ሙሉ ለሙሉ ለቃ ከመውጣቷ በፊት ለአጋሮቿ የገባችውን ቃል ትፈፅማለች” ብለዋል ባሪሶቭ።

ሞስኮ የራሷን የጠፈር ጣቢያ ማቋቋም ቅድሚያ ከምትሰጣቸው ተግባራት አንዱ መሆኑን ግልፅ አድርጋለች።

የዩናይትድ ስቴትስ የጠፈር ተቋም ሩሲያ ከዓለም አቀፉ የጠፈር ምርምር ጣቢያ እየወጣች ስለመሆኑ እንደማያውቅ አንድ የናሳ ከፍተኛ ባለሥልጣን ለሮይተርስ መናገራቸው ተዘግቧል።

የሩሲያው ውሳኔ የመጣው ዩክሬንን በመውረሯ ምክንያት በምዕራባውያንና በመስኮብ መካከል ከፍተኛ ውጥረት በሰፈነበት ወቅት መሆኑም ተመልክቷል።