በድጋሚ የታደሰ
ሩሲያ ለአፍሪካ በነፃ ለመላክ ቃል ከገባችው እህል መጀመሪያው ጭነት መውጣቱን የግብርና ሚኒስትሯ ድሚትሪ ፓትሩሼቭ ዛሬ (ዓርብ) አስታወቁ።
ሃያ አምስት ሺህ ቶን ወይም 250 ሺህ ኲንታል እህል የጫኑ ሁለት መርከቦች ከሩሲያ ወደቦች መነሳታቸውንና በያዝነው ኅዳር መጨረሻ ሶማሊያና ቡርኪና ፋሶ ይደርሳሉ ብለው እንደሚጠብቁ ሚኒስትሩ መናገራቸውን የሃገር ውስጥ መገናኛ ብዙኃንን ጠቅሶ የፈረንሣይ የዜና ወኪል ዘግቧል።
ለስድስት የአፍሪካ ሀገሮች 200 ሺህ ቶን ወይም 2 ሚሊየን ኲንታል እህል በነፃ ለመላክ ፕሬዚዳንት ቭላዲሚር ፑቲን ሐምሌ ውስጥ ቃል ገብተው እንደነበር ኤኤፍፒ አስታውሷል።
የፕሬዚዳንቱ እህል የመላክ የተስፋ ቃል የመጣው ሞስኮ የዩክሬን እህል ከደቡብ ጥቁር ባህር ወደቦች ደኅንነቱ ተጠብቆ እንዲወጣ ካስቻለው በመንግሥታቱ ድርጅት አደራዳሪነት ተደርሶ ከነበረው ስምምነት ከወጣች በኋላ ነው።
ማስረጃ ባታቀርብም ከዩክሬን ወደ ውጪ የሚላከው እህል ወደ ድኃ ሀገሮች አይሄድም ወይም አይደርስም ስትል ሩሲያ ቅሬታና አቤቱታ ታሰማ እንደነበርም የኤኤፍፒው ዘገባ አመልክቷል።
ሩሲያና ዩክሬን በዓለም ግዙፎቹ እህል አምራችና ላኪዎች ናቸው።
ሩሲያ በዩክሬን ላይ እያካሄደች ያለችው ጦርነት በዓለም ዙሪያ የምግብ እጥረት እና በተለይም በእህል ምርቶች ላይ የዋጋ ንረት እንዳያስከትል ስጋት አሳድሮ ቆይቷል።
ተጨማሪ እህል ወደ መካከለኛው አፍሪካ ሪፐብሊክ፣ ኤርትራ፣ ማሊና ዚምባብዌ ከዓመቱ መጨረሻ በፊት እንደሚላክ ፓትሩሼቭ ተናግረዋል።
ፕሬዚዳንት ፑቲን በየካቲት 2014 ዓ.ም. ዩክሬን ላይ ሙሉ ወታደራዊ ዘመቻ ከከፈቱ በኋላ አፍሪካ ውስጥ የሚያደርጉትን ዲፕሎማሲያዊ ግፊት አፋጥነዋል።
ፑቲን ባለፈው ሐምሌ አጋማሽ ግድም ትውልድ ከተማቸው ሴንት ፒተርስበርግ (ሳንክት ፒተርቡርግ) ውስጥ ሁለተኛውን የሩሲያ-አፍሪካ መሪዎች ጉባኤ ያስተናገዱ ሲሆን የሩሲያን ጦር መሣሪያ አምራቾችና በመንግሥት የሚመራውን የኒኩሌር ኃይል ኩባንያ ትርዒቶችንም አስጎብኝተዋል።