ሩሲያ በከፍተኛ ጀኔራሏ ግድያ የተጠረጠረውን ግለሰብ መያዟን አስታወቀች

የሩስያ የኑክሌር ባዮሎጅካዊ እና ኬሚካል መከላከያ ኃይል ዘርፍ አዛዥ የነበሩት ጄኔራል ኢጎር ኪሪሎቭ

ሞስኮ ውስጥ በተገደሉት ከፍተኛ ጀኔራል ግድያ የተጠረጠረው ግለሰብ የኡዝቤክስታን ዜግነት ያለው መኾኑን የገለጽው የሩሲያ ደኅንነት ተቋም፣ በዩክሬን የስለላ ተቋም የተመለመለ መኾኑንም አስታውቋል።

ሩሲያ የግለሰቡን ስም ባትገልጽም እ.አ.አ በ1995 እንደተወለደ ይፋ አድርጋለች፡፡ ግለሰቡ በዩክሬን የደኅንነት ተቋም እንደተመለመለ መናገሩንም የሩሲያ የደኅንነት ተቋም አስታውቋል። ግለሰቡ በምን ሁኔታ ውስጥ ሆኖ ለፀጥታ ተቋሙ ቃሉን እንደሰጠ ማረጋገጥ እንዳልቻለ አሶስዬትድ ፕረስ በዘገባው አመልክቷል።

ጀኔራል ኢጎር ኪሪሎቭ ትላንት ማክሰኞ የተገደሉት ከሚኖሩበት ሕንጻ ውጪ ባለሁለት ጎማ ተሽከርካሪ (ስኩተር) ውስጥ በተደበቀ ቦምብ ነበር። የጀኔራሉ ረዳትም በፍንዳታው መገደላቸው ታውቋል።

እንድ የዩክሬን ባለሥልጣን ግድያው በሀገራቸው የስለላ ተቋም መፈጸሙን ተናግረዋል። ጄኔራሉ የተገደሉት የዩክሬን የደኅንነት ተቋም የወንጀል ክስ ካቀረበባቸው ከአንድ ቀን በኋላ ነው።