የሩሲያ ፕሬዘዳንታዊ ምርጫ እየተካሄደ ነው

  • ቪኦኤ ዜና
ከሞስኮ በምስራቅ 2236 ኪሜ (1397 ማይል) ርቃ በምትገኘው በሳይቤሪያ ኦምስክ ከተማ ለፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ግለሰቡ ድምጽ ሲሰጡ ሩሲያ፣ አርብ እአአ መጋቢት 15 ቀን 2024

ከሞስኮ በምስራቅ 2236 ኪሜ (1397 ማይል) ርቃ በምትገኘው በሳይቤሪያ ኦምስክ ከተማ ለፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ግለሰቡ ድምጽ ሲሰጡ ሩሲያ፣ አርብ እአአ መጋቢት 15 ቀን 2024

ለሦስት ቀናት የሚደረገው የሩሲያ ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ዛሬ ዓርብ ሲጀምር፣ የቭላድሚር ፑቲን የሥልጣን ዘመን በስድስት ዓመታት እንደሚራዘም እርግጥ መሆኑ እየተነገረ ነው።

ምርጫው የሚካሄደው ፕሬዚዳንት ቭላድሚር ፑቲን ተቃዋሚዎቻቸውን ሁሉ ዝም ባሰኙበት ፣ በሀገሪቱ ገለልተኛ ሚዲያ እና የመብት ተቆርቋሪ ቡድኖችን በማሽመድመድ የፖለቲካ ሥርዓቱን በቁጥጥራቸው ስር ባደረጉበት እና ሩሲያ በዩክሬን ላይ የከፈተችው ጦርነት ሦስተኛ ዓመቱን ባስቆጠረበት ወቅት ነው።

በጦርነቱ ሩሲያ ቀስ በቀስም ቢሆን በየውጊያ ግንባሩ የበላይነቱን በመያዝ ላይ ነች፡፡ ዩክሬን በበኩሏ ሩሲያ ውስጥ ድረስ የሚዘልቅ የድሮን ጥቃት በማድረግ ሞስኮ ከአደጋ የተጠበቀች አለመሆኗን አሳይታለች፡፡

በአስራ አንድ የሰዓት ክልሎች በተከፈለችው ሩሲያ፣ ከዛሬ ዓርብ እስከ እሁድ ድረስ ድምፅ ሰጪዎች ወደ ምርጫ ጣቢያ ያመራሉ።

ምርጫው ልብ አንጠልጣይ አይሆንም። ለአምስተኛ ጊዜ ለምርጫ የቀረቡት ፑቲን ተፎካካሪ የላቸውም። የፖለቲካ ባላንጣዎቻቸው ታስረዋል አልያም ለስደት ተዳርገዋል። ዋናው ተቀናቃናቸው አሌክሲ ናቫልኒ በእስር ላይ ሳሉ በቅርቡ ሕይወታቸው አልፏል።

በምርጫው የሚሳተፉ ሦስት ሌሎች ተፎካካሪዎች ብዙም የማይታወቁ እና የክሬምሊንን ፖሊሲ የሚከተሉ ናቸው ተብሏል።