የሩሲያው ፕሬዝደንት ቭላድሚር ፑቲን በመጪዎቹ ቀናት የዓለም መሪዎችን በመቀበል የብሪክስን ጉባኤ ያስተናግዳሉ።
የቻይና፣ የሕንድ፣ የቱርክ፣ እንዲሁም የኢራንን ጨምሮ በርካታ የዓለም መሪዎች የሚገኙበትና በሩሲያዋ ካዛን ከተማ የሚካሄደው ጉባኤ፤ በዩክሬን በሚካሄደው ጦርነትና በወጣባቸው የእስር የመያዣ ትዕዛዝ ምክንያት ከዓለም መድረክ ይገለላሉ ሲባሉ የነበሩት ፑቲን፣ አሁንም ተሰሚነት እንዳላቸው ማሳያ ነው ተብሏል።
ሩሲያ የብሪክስን ጉባኤ በማስተናገድ፣ ከምዕራቡ ዓለም ጋራ ውጥረቱ እየቀጠለ ቢመጣም ከአጋሮቿ ጋራ መቆሟን ለማመልከት የምትጠቀምበትና የጦርነት ኢኮኖሚዋን ለመደገፍ ስምምነትና ድርድር የምታደርግበት መድረክ መሆኑን ተንታኞች በመናገር ላይ ናቸው። ለሌሎቹ ለተሳታፊ ሃገራት ደግሞ ትርክቶቻቸውን አጉልቶ ለማሰማት ዕድል የሚሰጥ መድረክ ነው ተብሏል።
ነገ ማክሰኞ ጉባኤውን የሚጀምረውና በማደግ ላይ ያሉ ኢኮኖሚዎች ስብስብ የሆነው ብሪክስ፤ በምዕራቡ ዓለም የሚመራውን የዓለም ሥርዓት ለመገዳደር በሚል ሲጀመር በአምስት ሃገራት የተቋቋመ ሲሆን፣ በያዝነው ዓመት ግን ኢትዮጵያን ጨምሮ በርካታ ሃገራት ተቀላቅለዋል። ሌሎች በርካታ ሃገራትም ለመቀላቀል ጥያቄ በማቅረብ ላይ ናቸው።