ዩክሬይን ውስጥ በሩሲያ ጥቃት 11 ሰዎች ሲገደሉ 89 ሰዎች ቆስለዋል

  • ቪኦኤ ዜና

በሩሲያ አየር ጥቃት የተጎዳ ህንፃ በሱሚ፣ ዩክሬን እአአ ኅዳር 18/2024

ሩሲያ ሱሚ በተባለች የዩክሬይን ሰሜን ምስራቃዊ ግዛት ባደረሰችው ጥቃት 11 ሰዎች ስትገድል ሌሎች ቢያንስ 89 ሰዎች ማቁሰሏን የዩክሬይን ባለስልጣናት ተናግረዋል፡፡

በጥቃቱ 90 የመኖሪያ ህንጻዎች እና 28 መኪናዎች፡ ሁለት ትምህርት ተቋማት እና 13 የመሥሪያ ቤት ህንጻዎች መጎዳታቸውን የዩክሬይን ባለስልጣናት ተናግረዋል፡፡

ትላንት እሁድም ሩሲያ በዩክሬይን የኃይል ማመንጫ መሠረተ ልማት ላይ ከባድ የቦምብ ድብደባ አድርሳለች፡፡

ይህ በዚህ እንዳለ ዩናይትድ ስቴትስ ዩክሬይን በረጅም ርቀት ተኳሽ የጦር መሣሪያዎቿ ሩስያ ግዛት ውስጥ ያሉ ወታደራዊ ኢላማዎችን እንድታጠቃ ፈቅዳለች የሚሉ የዜና ዘገባዎች በትላንትናው እለት ተሰራጭተዋል፡፡

ሩስያ ጦርነቱን አጠናክራ ለመቀጠል አስራ ሁለት ሺህ ሰሜን ኮሪያዊያን ወታደሮችን ማሰለፏን ተከትሎ ፕሬዚደንት ጆ ባይደን ዩክሬን ዩናይትድ ስቴትስ በሰጠቻት ረጅም ርቀት ተተኳሽ መሳሪያዎች እንድትጠቀም መፍቀዳቸውን አንድ የዩናይትድ ስቴትስ ባለስልጣን እና ሊሎች ስለጉዳዩ የሚያውቁ ሦስት ሰዎች ዋቢ አድርጎ አሶሲየትድ ፕሬስ ዘግቧል፡፡

ካሁን ቀደም ባይደን የዩክሬይኑን ጦርነት በይበልጥ መቀጣጠል ሲቃወሙ ቆይተዋል፡፡ ፑቲን በበኩላቸው የኔቶ አባል ሀገር ለዩክሬይን የሩሲያን ግዛት በጦር መሣሪያዎቹ እንድታጠቃ ቢፈቅድ እኛም ሌሎች አካላት ምዕራባዊያን ኢላማዎችን የሚመቱበት የረጅም ርቀት ተተኳሽ መሣሪያ ልንሰጥ እንችላለን ብለው እንደነበረ ይታወሳል፡፡